ኦርቶዶክስን በዘፈን መንቀፍ ግፍ ነዉ!

አክሊሉ ደበላ

ስለዘፈንም ሆነ ስካር፣ ስለ ሥነ ምግባርም ሆነ ትሩፋት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክንን ትሰማታለህ እንጂ አትነግራትም።  በግልፅ ድንበር ዘፈን ኃጥአት ሆኖ ንስሃ የሚያስገባዉ በኦርቶዶክስ ነዉ። ዝሙት ከመንግስተ ሰማያት ተሥፋ የሚያስቀር ሆኖ የሚሰበከዉ በኦርቶዶክስ ነዉ። ዉሸት ፅዩፍ ሆኖ የተኖረዉ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ነዉ። የማወራዉ እንደሚቆረቁርህ አዉቃለሁ። ግን እዉነቱን ቀስ ብለን እንዋጥ።

ባንተ ሃይማኖት ስካር ኃጥአት ሆኖ የሃይማኖትህ ቀኖና ሆኖ ሰምቼ አላዉቅም። ባይሆን የተሃድሰዉ መሥራች የእምነትህ ፋና ወጊ ቃል በቃል ሰይጣንን ለማናደድ ብሎ እንደሚሰክር ተናግሯል። በሕይወቱም ሁሉ ያኔ ከነበረዉ መጠጥ ከወይን ጋኖች ሥር ሳይጠፋ እስከ ሞቱ የደረሰ ሰዉ መሆኑን ብነግርህ ይከፋህ ይሆን?

በየትኛዉ የሃይማኖት ቀኖናችሁ ዘፈን ከሕይወት መዝገብ የሚለይ ሆኖ ተመዘገበ ይሆን? የምትድነዉ በፀጋ ሆኖ ሳለ ያንተ ዘፈን መስማት አለመስማት ምን እንዲጨምር ምን እንዲቀንስ ተብሎ ነዉ የዘፈን ዋጋ የሚረክሰዉ?

የኛ ሰዎች ዘፈን አይሰሙም ልትለኝ ነዉ?  ግድ የለም ይህም ዉሸት ነዉ!!

እስቲ ትንሽ መረጃ ሰብስብና ስለዘፈንም ሆነ ስለ መጠጥ፣ በገላትያ 5 ላይ ስለተዘረዘሩት የመንፈስ ፍሬዎች ሁሉ አንድ በአንድ የሃይማኖትህ ፍሬ ይሁኑ አይሁኑ ጎግልም ቢሆን ጠይቅ!

በዓለም ካሉት ሀገራት የእምነትህ ተከታዮች አብዛኛዉን ቁጥር የሚይዝ ሀገር ውስጥ :- ዘፈን የማዳመጥ መጠንን፣ ዝሙት የመፈፀም ቁጥርን፣ የሥካር አሃዝን ጠይቅና ተመለስ!! መልሱን በርግጥ ታዉቀዋለህ!
መልሰህም :_ ስለኛ እንጂ ስለነሱ አይመለከተኝም ትልም ይሆናል። 

አንድ ታሪክ እንያዝና የአንተ ሰባኪዎች በኛ ሀገር ለምን በነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ላሥረዳህ!

በጄኔቫ ከተማ ውስጥ ተንሠራፍቶ የነበረዉን የሌብነት፣ የጭካኔ፣ ና ሌሎች የሥነ ምግባር ጉድለቶችን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም እነዚህን የህብረተሰብ ደካማ ጎን በመንቀፍ ትምህርቱን ያስፋፋ ካልቪን የስዊዘርላንድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ኋላ የገዢዎቹን ትኩረት አግኝቶ የከተማ ኦፊሴላዊ ሃይማኖት አድርጎ አስፋፍቷል። ሆኖም የሃይማኖቱ ሥነ ምግባራዊ ይዘት ከዶግማዊ ትኩረቱ ጋር የተጣጣመ ስላሆነ በጊዜ ሂደት Fade እያረገ ሄዶ ዛሬ ዝዊንጊ ባሥተማረበት ዙሪክ ከተማ  ትምህርቱ ከእሴቱ ተላቋል። አላማዉም የነበረ  Strategic መሣሪያነት እንጂ ሃይማኖታዊ አቋም አይደለምና።

ወደኛ ሀገርም ሲመጣ፣ ወደ ሌሎችም ሀገሮች:- እነዚህ የሚነገሩ የኃጥአት ዝርዝሮች ሰዉን ከነበረበት እምነት ማስኮብለያ ናቸዉ። ባይሆን ኃጥአት መሥራት ከተሥፋ መንግስተ ሰማያት የሚያስቀረዉ ለእኛ ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነዉ።

ለእኛ ዘፈን ኃጥአት ነዉ። የምርም ኃጥአት ነዉ። ንስሃ ግን ያጥበዋል። በዚህ ኃጥአት ዉስጥ ለወደቀ ልባችንም ከሲራክ ጠቅሰን "ልጄ ሆይ ስለ ኃጥአትህ ብለህ ንስሃ መግባትን አትፍራ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቸርነት ብዙ ነዉ እያልክ በኃጥአት ላይ ኃጥአትን አትሥራ" እንላለን።

ባይሆን ከዚህ ኃጥአት የሚከፋብን ከሃይማኖት የወጣዉን ድምፅ መስማት ነዉ። የነዉር ሁሉ ነውር ሥግዉ ቃል ክርስቶስን "አማላጅ" ብሎ የሚገልጠዉን ዜማ እንደ 'ወንጌል' መስማት ነዉ። ለዘፈንስ ንስሃ ሳሙናዉ ነዉ። ይህ ድምፅ ግን ክህ*ደት ነዉና መንፈስ ቅዱስን እነደተሳደበ ሥረየት የለዉም። ከዘፈንም ይልቅ የሚዘንነን በየመንገዱ አማናዊ ያልሆነዉን "ኢየሱስ"  ለመስበክ ስትለፉ ነዉ። ነቢያቶችህና ዘማሪዎችህ የነዚህን ዘፋኞች ዜማ ሳይቀር እየሰረቁ መዝሙር የሚያወጡልህ እኮ ሰምተዉ ነዉ። በዚህም ቢያንስ ሦስት ኃጥአት ይፈፅማሉ። 1.የተከለከለዉን ዘፈን ይሰማሉ 2.የሰዉ የሆነዉን ይሰርቃሉ 3.እንደራሳቸዉ አድርገዉ በማሰማት ይዋሻሉ። በዚህም ከኦሪትም ከወንጌልም ህግ ያፈነግጣሉ። 

ባይሆን የግብዝነት ስብከት እንዴት አስጠሊታ እንደሆነ በምን ቃል ልንገርህ? የማትኖረዉን መናገር፣ የማትሆነዉን ማሳየት፣ ንፅፅርና ሁሉ ነገር ላይ የከበረ የክርስቶስ ስምን እንደ ዝንብ ጥልቅ ማድረግ ምን ያህል ክብረ ቢስነት እንደሆነ በምን ቃል ልንገርህ? እንዲህ ባደረግህ ቁጥር ክርስትና እንዴት እንደምትጠላ ከማሰብ በቀር ምን እላለሁ? ምናልባትም ተልእኮህም በዓለም ክቡር የሆነዉን የክርስትና እምነት ከሰዎች ልቦና አውጥቶ የተዋረደና እምነት አልባ ህዝብ መፍጠር ቢሆንስ ብዬ እሰጋ እንደሆነ እንጂ ቅንጣት ታክል የክርስቶስ መንግስት ሰባኪ እንደሆንክ ማሰብ አልችልም። ላከበረህ አምላክህ ክብር እንኳ የማትራራ እንደሆነ ነገረ ሥራህ ይነግረኛልና።

Post a Comment

0 Comments