ዘፈን ኃጢአት ነው?

  ተመስገን ደምሰው ግዛው

ስለ ዘፈን ያለው አመለካከት እንደ ዘፈኑ ይዘት ይለያያል። አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት የሚሰጠው በቃላቱና በመልእክቱ ላይ ነው። ጥላቻን፣ ዝሙትን ወይም ክፉ ድርጊቶችን የሚያበረታቱ ዘፈኖች እንደ ኃጢአት ይታያሉ። ይሁን እንጂ ፍቅርን፣ ሀገርን እና ሰብአዊነትን የሚገልጹ ሥራዎች እንደየአውዳቸውና እንደ አመለካከቱ ይወሰናሉ።

አንድ ዘፈን ኃጢአት መሆን አለመሆኑን ለመወሰን ብዙዎች የሚከተሉትን መስፈርቶች ይመለከታሉ፦

ቃላቱ፦ ስድብ፣ ጸያፍ ንግግሮች ወይም ሰውን የሚያቃልሉ መልእክቶች ካሉት እንደ መጥፎ ነገር ይታያል።

ተጽዕኖው፦ ዘፈኑ አድማጩን ወደ መጥፎ ድርጊት የሚገፋፋ ከሆነ እንደ ኃጢአት ሊቆጠር ይችላል።

ዓላማው፦ ለደስታ፣ ለሰላም፣ ለትምህርት ወይም ለባህል መግለጫ የሚሆኑ ዘፈኖች በአብዛኛው እንደ በጎ ነገር ይታያሉ።

በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ ዘፈን የባህል መግለጫ፣ የጭንቀት ማስታገሻ እና የታሪክ ማስተላለፊያ መንገድ ነው። ለምሳሌ የሀገር ፍቅር ዜማዎች ወይም ስለ ሥራ ጥንካሬ የሚያነሳሱ ዘፈኖች እንደ ጠቃሚ ሥራዎች ይወሰዳሉ። ስለዚህ ጉዳዩ በቀጥታ "አዎ" ወይም "አይደለም" ተብሎ የሚደመደም ሳይሆን እንደ ይዘቱ የሚወሰን ነው። ሕሊናህ የማይቀበለውን ወይም ከፈጣሪ ጋር ያለህን ግንኙነት የሚያሻክር መስሎ የሚሰማህን ዘፈን አለመስማት የተመረጠ ይሆናል። በአንጻሩ ወደ በጎ ነገር የሚመራ መልእክት ካለው "ኃጢአት ነው" ማለት አይቻልም።

ከዚህ አንጻር ስለ ጽዮን፣ ስለ ሀገር ባንዲራ እንዲሁም ክፉ ገዥዎች ክፉ ድርጊታቸውን እንዲተዉ የሚናገር መልእክት ያለው ዘፈን የሚያስመሰግን ነው። በእርግጥ ይህንን ተግባር ካህናት፣ ዘማርያን፣ ሰባኪያንና ባሕታውያን ሊሠሩት የሚገባ ቢሆንም፤ ጊዜያዊ የሥጋ ኑሮ ስለበለጠባቸው አፋቸውን ለጉመው ተቀምጠዋል።

መለስ ዜናዊ "ጨርቅ ነው" በማለት ያቃለለውን ባንዲራ፣ አባ ገብረ ኪዳን ኮራ ቀብረር ብለው ደግመውታል። የማኅበረ ቅዱሳን ቀንደኛ መሪ ብርሃኑ አድማሱም መለስ ባዋረደው ልክ አዋርዶታል። ብዙ ሰባኪዎች በስብሰባ የወሰኑት እስኪመስል ድረስ ባንዲራውን ከሕዝብ ልብ ለመፋቅ የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። እነዚህ ሰባኪዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ ጣሊያን የኢትዮጵያን ባንዲራ አውርዶ የራሱን ቢሰቅል "ጨርቅ ነው" በሚል ሰበብ ችግር የለውም እያሉ በአቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ላይ እየተሳለቁ ነው።

በነገራችን ላይ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ ፍርድ የፈረዱት ሆዳም ካህናት ነበሩ። ዛሬም ባንዲራን "ጨርቅ ነው" እያሉ የሚያቃልሉት የባንዳ የልጅ ልጆች ናቸው። እነዚህ ሰባኪያን ባንዲራን "ጨርቅ ነው" ባሉበት አንደበታቸው፣ ትእዛዝ ከተሰጣቸው "መስቀሉ እንጨት ነው" ለማለት እንደማይመለሱ ጥርጥር የለውም። ከዚህ አኳያ ከብዙ ሰባኪያን ይልቅ ቴዲ አፍሮ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በድፍረትና በሞት መካከል ሆኖ እውነትን ተጋፍጧል ማለት ይቻላል። ቴዲ አፍሮ የተጋፈጠው የዘመኑ ባሕታውያን የፈሯትን ሞት ነው።

ቴዲ አፍሮ አንሳው ያለህ የዘመኑ ካድሬ ሰባኪያን ከጠላቶቻችን ጋር ሆነው ያስጣሉንን አጱነ ጴጥሮስ የሞቱላትን ሰንደቅ-ዓላማ ነው።

Post a Comment

0 Comments