ነብር ነበር ድሮ በግ ኾኖ አረፈው ኮሪያዊው ዘንድሮ


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታ

ጀግና፣ ደፋር፣ ቆራጥ የነበረው ኮርያዊ ከተጋተዉ ልብ አጥፊ ትርክት የተነሳ ሽቅርቅር፣ ቅብጥብጥ፣ ቅልጥልጥ፣ ሽልጥልጥ ኾነ!

(ስለ ኮርያ ከዚህ በፊት የጻፍኳቸውንም አንብቡ)

የአንድን ሕዝብ ወታደራዊ ግርማና አርበኛዊ ወኔ ለመስለብ የጦር ሠራዊት ከማዝመት ይልቅ ትውልዱን በረቂቅ ትርክት መስለብ፣ ማሞከት በቂ ነው።

እ.ኤ.አ. በ1943 ዓ.ም. ኮሪያ በኮሚኒስት ወረራ ስትፈተን፣ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለሽንፈት የማይመቸውን የ”ቃኘው” ሻለቃ ጦር በመላክ ከኮሪያውያን አርበኞች ጋር አብረው ደማቸውን አፍስሰዋል። ያኔ ኮሪያዊው ወንድ ከኢትዮጵያ አንበሶች ጋር ትከሻ ለትከሻ ተያይዞ ለነፃነቱና ለክብሩ ሲል በቆራጥነት የሚፋለም “የእስያ ነብር” ነበረ።

ይህ ስልታዊ የወንድነት የሥነ-ልቦና ስልባ (ማኮላሸት) ግን የጥንቱን የጀግንነት ታሪክ በማጠልሸትና ወንዱን በባሕሪው “ጥገኛና ደካማ” አድርጎ በሚሰብከው የ”ሳዳ-ጁዊ” ትርክት ተተካ።

ጃፓን በወረራ ዘመኗ የጀመረችው የታሪክ ብረዛ፣ ኮሪያዊው ወንድ ለጦር ሜዳና ለሀገር ጥበቃ የማይመጥን ምን ቢማር “እንከፍ፣ ምስኪን” እንደኾነ አድርጋ በመሳል፣ ትውልዱ ራሱን እንደ “አድራጊ” ሳይኾን “አደግዳጊ፣ ተላላኪ፣ ጃንደርባ” እንዲቆጥር አደረገችው።

ያኔ ከቃኘው ሻለቃ ጋር በቆራጥነት የቆመውና ለዓለም የኅብረትና የአንድነት ምሳሌ የኾነው አርበኛዊ ወኔው፣ ዛሬ በዘመናዊ መልክ ተቀይሮ ወንድነቱን በኮርያ ፊልምና ዘፈኖች ላይ እንደምታዩት በውበትና ታይታን በፈለገ ቅብጥብጥ ባሕሪ ብቻ በመለካት የጀግንነት እሳት ሙቀቱን፣ የወንድነት ወኔ ድፍረቱን አጥፍቶበታል።

በተለይ በዚህ ዘመቻዋ አባወራዊ ወኔ የነበረውን ኮርያዊ ወንድ ዳግም ማንሰራራት ከማይችልበት ልባልባነት፦ መሪነቱን፣ ጠባቂነቱን ኮንና አደረሰችው።

ትውልዱን ከመጣበት እሴቱ፣ ዘርን ካስቀጠለ ትውፊቱና ለኑሮ ከሚታጠቀው ድፍረቱ ለይቶ “ልባልባ” የማድረግ ሂደትም መጨረሻው ምክነት ነው።

ዛሬ ኮሪያዊው ወንድ ሽቅርቅርና ቅብጥብጥ ኾኖ በዓለም አደባባይ ቢታይም፣ በመንፈስ ግን ተስፋ የቆረጠ፣ ሳይዋጋ የተሸነፈና ለሀገሩ ዘላቂ ሕልውና ግድ የማይሰጠው ኾኗል።

ወንድነቱ በስልብ ጃንደርባ ባሕሪ ሲተካ፣ ቤተሰብና ማኅበረሰብን ለማስቀጠል የሚፈልገውን ወኔ፣ ለሀገርና ለቤተሰብ መሪነት የሚጠይቀውን መስዋዕትነትና ኃላፊነት የሚሸከምበት “የነብር ልቡ” ተፍቷል።

በዚህም ምክንያት ኮሪያ ዛሬ በዓለም ዝቅተኛው የወሊድ መጠን ባለቤት ኾና ማንም በጦር ሠራዊት ሳይዘምትባት ራሷን ለባዕድ አሳልፋ መስጠት ግድ ኾኖባታል።

ደቡብ ኮርናያ የአንድን ማኅበረሰብ የጀግንነት ታሪክ እየኮነኑና እሴቱን እያረከሱ ትውልዱን መጋት፣ ራሱን በራሱ የሚሰልብበትን ካራ በእጁ እንደመስጠት እንደኾነ ሌላኛዋ አስረጅ ናት።

ጀግናን ማኮሰስ መጨረሻው ሕዝብ የሚቆምለት፣ የሚዋደቅለት ክብር እንዳይኖረው አድርጎ መስለብ፤ በዚያም ማኅበረሰቡን ማስደፈርና ማምከን ነው።

ኮሪያዊው ወንድ ከጥንታዊው ግርማው ወጥቶ ወደ በግነት የተቀየረው፣ የታሪክ ጸሐፊውና የባዕድ ትርክት አሳላፊው ጀግኖቹን “በሞራል ክለሳ” ስላጠቁበት ነው።

የዛ ሁሉ የጀግኖች ታሪክ፣ የታሪክ ድርሳናት ምስክርነት፣ የነ ሆሜርና ሄሮድትስ ምስክርነት የት ገባ? ማን በእንዴት ዓይነት መሰል ትርክ ሰለበው?






Post a Comment

0 Comments