ወኔው ለተሰለበ ትውልድ መሃንነቱም እውን ይኾናል!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታ

ጠላት ልባልባ አልያም ሆዳደር ሊቃውንትን ተጠቅሞ የትውልዱን የእሴት ትርክት ራስ ጠልነትን ወደሚያስከትል አሳፋሪና አሸማቃቂ ሲቀይረው ትውልድ ይጠፋል ማኅበረሰብም ይመክናል! ሥነ-ልቦናዊው ስልበት ጃንደርባ ትውልድ ያፈራል!

“ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የአንድ ሕዝብ ውድቀት የሚጀምረው በድንበር መጣስ ሳይኾን በልብ መሸበር ነው። ጠላት የራሱን አጀንዳ ለማስፈጸም “ሆዳደር” ሊቃውንትንና “ልባልባ” ምሁራንን እንደ መሣሪያ በመጠቀም፣ የትውልዱን አርበኛዊ ታሪክና ኩሩ እሴት በ”ሞራል ክለሳ” ካራ ይፍቀዋል።

ትውልዱ ስለ አባቶቹ ጀግንነት ከመኩራት ይልቅ በታሪኩ እንዲያፍር፣ በራሱ እንዲጠራጠርና በ”ጥፋተኝነት” ሰንሰለት እንዲታሰር ሲደረግ፣ በውስጡ ያለው የአንበሳ ግርማ፣ የወንድነት ወኔ ይሞታል።

ይህ ሥነ-ልቦናዊ ስልበት ደግሞ ውጤቱ የሥነ-ልቦና ጃንደርባ መኾን ብቻ ሳይኾን፣ ወደ አካላዊ(ባዮሎጂያዊ) መካንነት (Infertility) የሚያመራ አደገኛ መርዝ ነው።

ሳይንሳዊው ጥናቶች እንደሚነግሩን በራስ-ጠልነት፣ በአባቶቹና በወንድነት ተፈጥሮው የሚሸማቀቅ ትውልድ የእድገ ንጥር(hormone) ሥርዓቱ ይቃወሳል፤ የወንድነት ግርማው ይከስማል፤ የዘር ጥራቱም ይላላል(ይሳሳል)።

የወንድነት ወኔ፣ የሊቢዶ (Libido) እና የዘር ጥራት መሠረቱ Testosterone ሆርሞን ነው። አንድ ትውልድ በታሪኩ እንዲያፍር፣ በራሱ እንዲጠራጠርና በ”ጥፋተኝነት” (Guilt) ስሜት እንዲሸማቀቅ ሲደረግ፣ ሰውነቱ ከፍተኛ መጠን ያለው Cortisol (የውጥረት ሆርሞን) ያመነጫል።

በሰውነታችን ውስጥ Cortisol የተባለው በጭንቀት ጊዜ የሚመነጨው እድገ ንጥር ሲነግሥ፣ የወንዴዘሩ Testosterone በከፍተኛ ኹኔታ ይወርዳል።

ይህ የእድገ ንጥር(hormone) ሲቀንስ ደግሞ የወንድ ልጅ የመራባት አቅም የወንዴ ዘሩ ልምላሜ (Sperm quality and count) አብሮ ይከስማል።

ትውልዱን በ”ጥፋተኝነት” መቀጥቀጥ ማለት በሥነ-ልቦናዊው ተጽዕኖው አካላዊ(bilogical) በኾነ ደረጃም ወንድነቱን “መሰለብ” (Chemical Castration) ማለት ነው።

አንድ ወንድ “የማልረባ ነኝ”፣ “አባቶቼ ጨካኝ ነበሩ”፣ “እሴቶቼ ኋላቀር ናቸው” የሚል ትርክት ተግቶ ሲያድግ፣ ንዑስ አእምሮው (Subconscious) የመሪነትና የአባወራነት ሚናውን ውድቅ ያደርገዋል።

ይህ ሥነ-ልቦናዊ ስብራት ወደ አካላዊ መዛባት ይቀየራል። የፍላጎት ማጣት (Low Libido) እና ለትዳርና ለዘር ቀጣይነት ግድየለሽ መሆን ይከተላል።

አዎን፣ አንድ ትውልድ በራሱ ላይ እምነት ካጣና “ባልፈጠር ይሻል ነበር” የሚል የጥፋተኝነት ክስ በመላ ሰውነቱ ከተሰራጨበት፣ በተፈጥሮ ያለው የመራባት ልምላሜ፣ የመራባት ፍላጎቱና አቅሙም ይኮላሻል።

ዛሬ በምዕራቡ ዓለምና በምሥራቅ እስያ የሚታየው ከፍተኛ የመካንነትና የወሊድ መጠን መቀነስ፣ ከኢኮኖሚው ይልቅ ከዚህ ከሥነ-ልቦናዊ ስልበት ጋር የተያያዘ ነው።

ልቡን በዚያም ያለ ወኔውን፣ በገለጫ ስሜቱን የሰለብነውን ትውልድ “ለምን ዘር አይተካም?” ብሎ መጠየቅ ሞኝነት ነው። ዘር የሚተካው ለነገ ተስፋ ያለው፣ በራሱ የሚተማመንና “የምኖረው ለታላቅ ዓላማ ነው” ብሎ የሚያምን ወንድ ነው።

በራስ-ጠልነት የተመረዘ፣ ማንነቱን በጥፋተኝነት የከሰሰ ትውልድ፦ ራሱን የሚጠላ ሰው ሌላ ሕይወት የመፍጠር (Procreation) ፍላጎት አይኖረውም። ይህ መሃንነት ታሪክን ከማክሸፍ፣ ትውፊትን ከማጨናገፍ የሚመነጭ በተለይም ወንዶችን የሚያጠቃ እኔ “ባሕላዊ ምክነት” Cultural Castration የምለው ነው።

የሽልጥልጥ ባሕሪ የሰፈነበት ጃንደርባዊ ትውልድ፣ ለነገ ተስፋ ስለማይኖረውና ለቤተሰብ መሪነት አባወራ የሚኾን ወኔ ስለሚታጣው፣ የሚኖርበት ማኅበረሰብ በገዛ እጁ መምከንን ይመርጣል፤ ይህንንም ከመንፈሳዊነት ቆጥሮ “እኛ የምንወርሰው ሀገር የለንም፤ ሀገራችን በሰማይ ነው እያለ ይመጻደቃል”።

ዛሬ በታሪክ ክለሳ ስም የአርበኝነትን እሳት የሚያጠፉ፣ የጀግኖችን ገድል የሚያኮስሱ “ሊቃውንት”፣ ትውልዱን ለባርነት ከማመቻቸት ባለፈ፣ የሕዝቡን ቁጥርና ጥራት የሚበላ “የጃንደርብነት ተውሳክ” እያሰራጩ እንደኾነ ልብ ሊባል ይገባል።

ጀግናን ማኮሰስና እሴትን ማራከስ መጨረሻው ትውልድን ማኅበረሰብን ማስደፈርና ሀገርን ማምከን ነው። ትውልዱ ከመጣበት ትውፊቱ ተቆርጦ በታሪኩ እንዲሸማቀቅ ከተደረገ፣ ውጤቱ ወንድነትን የናቀና ለዘር ቀጣይነት ግድ የማይሰጠው መካን ማኅበረሰብ መፍጠር ነው።

ይህ ደግሞ እስከዛሬ እንዳየነው በተለይ በመንፈሳዊ ተቋማት በኩል ይበልጥም “ጽድቅ ነው” በሚል ካባ camouflage ሲመጣ ለጥፋቱ መጠን መስፈሪያ መቁጠሪያ ያሳጣዋል!(ጥፋቱ እጅግ ይከፋል)

ለዘመናት በራስ-ጠልነትና በታሪኩ የውርደት ትርክት የተደበደበ ትውልድ፣ በተፈጥሮአዊ አካሉ በእርግጥ የመመከን ዕድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው።

የዘር ጥራት የሚጀምረው ከጠንካራ ሥነ-ልቦናና ከታሪካዊ ኩራትም ነው። በራሱ የሚከራ ትውልድ የሚኮራበትን ዘር ያስቀጥል፣ ያወርስ ዘንድ በተስፋ ይዘራል።

ታሪኩን የሰለቡት፣ ራሱን እንዲጠላ የሰበኩት፣ በአባቶቹ እንዲያፍር ያደረጉት ትውልድ ደግሞ ዘሩን እንዲያመክን በመንፈሳዊነት ስም ባጸደቁለት የጃንደርባ መንገድ ሄዶ ይጠፋል።

ስለዚህ አርበኝነትን፣ አባትነትን እና አባወራነትን መዘከሩ፤ አንድም ጀግንነትን፣ ድፍረትን፣ ተዋጊነትን ማስታወሱ የታሪክ ኩራት ለሀገር ክብር ብቻ ሳይኾን፣ ትውልድን ለማስቀጠል የተስፋ ችቦ፣ የልምላሜም ፋና ወጊ ናቸው። ይህንን “ሥነ-ልቦናዊ ስልበት” መከላከል ማለት የሕዝብን ቁጥርና የሰውነት ጥራቱን መጠበቅ ማለት ነው።

Post a Comment

0 Comments