ሴቷን ወደ መሪነት፤ ቤተሰብን ወደ ምክነት


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

ሴቶችን ወደ ተቋማት መሪነት ማምጣት ለዘመናዊው ዓለም “እኩልነት” ሊመስል ይችላል። ዓላማው ግን የማኅበረሰቡን የመከላከያ ግንቦች (ባሕልንና ሃይማኖትን) ሰብሮ በመግባት፣ ትውልዱን ያለ ጠባቂና ያለ መሪ ማስቀረት ነው።

በዘመናዊው የዓለም የፖለቲካና የማኅበራዊ መሐንዲሶች “ቤተመኩራ” የኾነው ማኅበረሰብ ውስጥ፣ “እኩልነት”፣ “አካታችነት” እና “መብት” የሚሉ ቃላት የነፃነት መፈክሮች ሳይኾኑ፣ የቆየውንና የጸናውን የማኅበረሰብ መዋቅር መፍረሻ መሣሪያ መዶሻዎች ኾነዋል።

በተለይም ሴቶችን ወደ መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት መሪነት የማምጣቱ ኹለንተናዊ ዘመቻ፣ ከበስተጀርባው የረቀቀና አደገኛ የኾነ “የግራምሺያኖች” (Gramscian) ሸፍጥ ያረገዘ፣ የትውልድ ጥፋትንና ምክነትን የሚወልድም መኾኑ ማወቅ ያስፈልጋል።

ይህ ሸፍጥ ሴቷን ከፍ ለማድረግ ሳይኾን፣ ማኅበረሰቡን ከሥሩ የሚደግፈውን የቤተሰብ ምሰሶ ነቅሎ፣ ከሥር መሠረት እሴቱም መንግሎ ለመጣል የታለመ ነው።

፩ኛ ከተፈጥሮአዊ ሚና የማፈናቀል ስልት

አንዲት ሴት ሚስትነቷንና እናትነቷን ትታ ወደ ቢሮክራሲያዊ መሪነት እንድትመጣ የሚደረገው ግፊት፣ በመጀመሪያ የሚመታው ቤቷን ነው።

ተፈጥሮ ለሴቷ የሰጣት ታላቅ ጸጋ “ቤትን መሥራት” እና “ትውልድን መቅረጽ” ነው። ይህ ሚናዋ ግን በዘመናዊው ትርክት እንደ “ኋላቀርነት” እና “እስረኝነት” ተደርጎ ይሳላል።

ሴቷን ከመኖሪያ ቤቷና ከባሏ ጋር ቤታቸውን ከምትሠራበት ተፈጥሮአዊ ሚናዋ ማራቅ፣ ቤተሰቡን ያለ ጠባቂና ያለ አስተማሪ ማስቀረት ነው። ቤቱ ባዶ ሲኾን፣ የልጆቹ ቀራጭ ወላጅ ሳይኾን መንግሥታዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ይኾናሉ። ይህ ደግሞ ቤተሰብን የማፍረሻው የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

፪ኛ የመንፈስና የዓላማ ምክነት

በሁለተኛ ደረጃ፣ ይህ ሸፍጥ በባልና በሚስት መካከል የአካል ብቻ ሳይኾን የመንፈስ ልዩነትን ይፈጥራል። “እኩልነት” በሚል ስም ሴቷ በቢሮክራሲያዊ የሥልጣን እርከን እንድትወጣ ሲደረግ፣ በቤት ውስጥ የምክክርና የመደጋገፍ መንፈስ በፉክክርና በሥልጣን ሽኩቻ ይተካል።

ባልና ሚስት በአንድ ጣራ ሥር ቢኖሩም፣ ዓላማቸውና መንፈሳቸው የተለያየ ይኾናል። ሴቷ የራሷን “መሪነት” ለማረጋገጥ ስትጥር፣ ባሏን እንደ አጋር ሳይኾን እንደ ተቀናቃኝ እንድታየው ትገፋፋለች።

ይህ የመንፈስ መለያየት በትዳር ውስጥ ያለውን ቅዱስ የኾነ ሕብረት፣ አንድነት፣ ውሕደት ከመፍጠር ይልቅ በመግደል፣ ቤተሰቡን ለውጭ ርዕዮተ-ዓለማዊ ጥቃቶች የተጋለጠ ያደርገዋል።

🚨 በዘመናችን የተስፋፋው እጅግ አስከፊውን ፍቺ ልብ ይሏል!

🌟 ሴት ሳይጠፋቸው መተማመን ከብዷቸው ትዳር መመሥረት ያቃታቸውን ምዕራባውያንን ተመልከት!





፫ኛ የትውልድ ቀጣይነትን ማምከን

የግራምሺያኖቹ እቅድ እጅግ አደገኛ የሚኾነው የትውልድ ቀጣይነትን በሚመታበት ነጥብ ላይ ነው። ሴቷ ወደ “መሪነት” እንድትመጣ ሲደረግ፣ የእናትነት ሚናዋ እንዲዘገይ ወይም እንዲቀር ይደረጋል። “ለሙያሽ (Career)፣ ለትምህርትሽ ቅድሚያ ስጪ” የሚለው ትርክት፣ እናትነትን እንደ ስኬት እንቅፋት አድርጎ ያቀርበዋል።

በዚህም የትውልድ መቀጠሉን ይስተጓጎላል፣ የማኅበረሰብ መስፋፋቱም ይመክናል። ይህ “ምክነት” ሥነ-ሕዝባዊ ብቻ ሳይኾን ባሕላዊም ነው። እናት የሌለበት ቤት፣ ታሪክና እሴት የማይተላለፍበት መካን ቤት ነው።

👉 ለዚህ አስተዋይ ዓይን፣ ሰሚም ጆሮ የለም እንጂ በጥፋት ቁልቁለቷ ላይ ወደ አዘቅቱ እየተምዘገዘገች ያለችውን እንግሊዝን ማየት ይቻላል!

፬ኛ አባወራነትን መሞገትና ማዳከም

“መሪ መኾን ትችያለሽ” ተብላ በየቀኑ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ በምንግሥት ፖሊሲ አውጪዎች፣ በሆዳደር የቤተክርስትያን ሊቃውንት የምትጋተው ሴቷ፣ ባሏን (አባወራውን) አጋዥና መሪ ከማድረግ ይልቅ፣ ሞጋችና ፈታኝ እንድትኾን ትደረጋለች።

የአባወራነት ጽንሰ-ሀሳብ እንደ “አምባገነንነት” ተፈርጆ እንዲጠላ ይደረጋል። ወንዱ ከመሪነትና ከጠባቂነት ሚናው ሲገፋ፣ ማኅበረሰቡ ዋነኛ የመከላከያ ግንቡን ያጣል። አባወራ የሌለው ቤተሰብ፣ አባት የሌለው ትውልድ ደግሞ ለጠላት እቅድ እጅግ አመቺ መጫወቻ ይኾናል።

👉 ለዚህ ደግሞ ደጋግመን ያነሳናቸው ጃፓናውያንና ኮርያውያንን የሚያክል አስረጅ አይገኝለትም።





፭ኛ የሴትነት ባህርይን ለጥፋት መጠቀም

በመጨረሻም ሴቶች ወደ መሪነት ሲመጡ በተፈጥሮአቸው ያላቸውን አዛኝነትና ርኅራኄ ጠላት ለራሱ ዓላማ ይጠቀምበታል።

“ሁሉን አቃፊነት” (inclusivity)፣ እና “የሰብአዊ መብት” በሚሉ ቃላት ሽፋን፣ ጠላት ትውልድን አጥፊና ሀገርን አፍራሽ የኾኑ ጽንሰ-ሀሳቦችን (ለምሳሌ፡ የግብረ-ገብነት መሸርሸርን) በሴቶች በኩል በቀላሉ ያስርጻል።

ሴቶች ስላሉበት “እንደ እናት ኾነው ያስቡልናል” ሲል ማኅበረሰቡ ጥርጣሬውን ይጥላል፤ ነገር ግን በዚያው ርኅራኄ ውስጥ የማኅበረሰቡን እሴት ከውስጥ የሚበላ መርዝ ይጋታል።

🚨 ሴቶችን በእኩልነት ሰበብ በቤተመንግሥትም ኾነ በቤተክርስትያን መሪነት ያመጡ ምዕራባውያን በተለይም እንግሊዛውያን በመንግሥት አስተዳደርም ኾነ በቤተክርስትያን እረኝነቱ በኩል ሀገራቸውን ማክሰራቸውን፣ ትውልዳቸውን ማምከናቸውን ማስተዋል ይገባል።

ሴቷን ወደ “መሪነት” የማምጣቱ የጩኸት ዘመቻ፣ ፍሬው ግን ቤተሰብን ወደ “ምክነት” መውሰድ ነው። ይህ ስልታዊ ሸፍጥ፣ ቤተክርስቲያናዊና መንግሥታዊ ተቋማትን ከውስጥ ገዝግዞ በመጣል፣ ትውልዱን ያለ ጠባቂና ያለ አባት ማስቀረት ነው።

በመኾኑም እውነተኛው ማኅበራዊ ፍትሕ የሚገኘው ሴቷን ከተፈጥሮአዊ ሚናዋ ነቅሎ ለቢሮክራሲያዊ ዓላማ መሣሪያ በማድረግ ሳይኾን፣ የቤተሰብን ቅዱስነት(sacredness) እና የአባወራነትን መሪነት በመጠበቅ ውስጥ ብቻ ነው።

ትውልዱ እንዳይጠፋ፣ ማኅበረሰቡም እንዳይመክን፣ ይህንን “የእኩልነት” ጭንብል የለበሰ የጥፋት እቅድ ነቅቶ መቃወም ጊዜው ከሚጠይቃቸው አርበኝነቶች አንዱ ነው!

መንግሥትም ኾነ ቤተክርስትያን ይህንን አጀንዳ ከምዕራባውያን ተቀብለው ሲያስፈጽሙ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንደሚያገኙበት ይታወቃል። ኾኖም ግን ነገ ሀገር፣ ማኅበረሰብ፣ ትውልድም እንዳይኖረን እያጠፉን እንደኾነ “ከአበራሽ ጠባሳ” ከምዕራባውያን መማር ይገባቸዋል።

🚨 ይህንን እያነበብን ዝም ለምንል ግን መጥኔ ለእኛ!

Post a Comment

0 Comments