አባወራው መር ቤተሰብ የትውልድ በተለይም የሴቶች እና የሕጻናት የአዛውንቱም መሰብሰቢያ፣ መከተቻ፣ መመሸጊያ ነው። እርሱ በፈረሰበት እነርሱ ለሥነ-ልቦናዊም ኾነ ለአካላዊ ጥቃት፣ ለመንፈሳዊ ሁከትም ይጋለጣሉ።
በአሁኑ ዘመን በከተሞችና በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የሚታየው ትውልድ፣ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ኹኔታ ግራ የተጋባና የቆመበት መሬት የራደው ይመስላል።
ይህ ትውልድ “የመቅበዝበዝ” ሰለባ ኾኗል ሲባል፣ መዳረሻ ስለሌለው ብቻ ሳይኾን የሚመለስበትና የሚያርፍበት “ምሽግ” ስለፈረሰበት ጭምር ነው።
በባህላዊውና በነባሩ ሥርዓት ውስጥ ቤተሰብ ለግለሰቡ ተራ የመኖሪያ አድራሻ ሳይኾን፣ ከውጫዊው ዓለም ማዕበል፣ ከርዕዮተ-ዓለም ጥቃትና ከማንነት ቀውስ የሚጠበቅበት ጠንካራ ምሽግ ነበር።
ይህ ምሽግ ደግሞ ያለ አባወራው መሪነትና ጠባቂነት ሊቆም አይችልም። አባወራው መር የኾነ ቤተሰብ መፍረስ ማለት፣ የምሽጉ ግንብ ተንዶ ለጥቃት ተጋላጭ መኾን ማለት ነው።
ዛሬ በከተማው ወጣት ዘንድ የሚታየው ስር የሰደደ የመጣው ጭንቀት፣ የባዶነት ስሜትና የፀረ-ድብርት መድኃኒቶች ሱሰኝነት፣ ይህ የጥበቃ ምሽግ መናዱ ያስከተለው ቀጥተኛ መዘዝ ነው።
ይህ እሴት ምሽጉ መፍረስ ሂደት በአጋጣሚ የመጣ ሳይኾን፣ “ነፃነት” እና “መብት” በሚሉ ማራኪ ቃላት በተሸፈነ ስልታዊ ዘመቻ የተከናወነ ነው።
በተለይም መንግሥታዊ ተቋማት፣ ዓለም አቀፋዊ የረድኤት ድርጅቶችና በዘመናዊነት ስም የሚነግዱ አካላት፣ የአባወራውን ሚና እንደ “ጭቆና” አድርገው በመሳል ሴቶችና ወጣቶች ከዚህ ምሽግ እንዲሸፍቱ (እንዲኮበልሉ) ሲገፋፉ ቆይተዋል።
“ከምሽጉ ውጡና ለብቻችሁ ቁሙ” የሚለው ቅስቀሳ፣ ሴቶችን ከመጠበቂያ ምሰሶአቸው ነቅሎ ለጨካኙ የገበያ ሥርዓትና ለብቻ የመታገል ሸክም አሳልፎ ሰጥቷቸዋል።
አንዲት ሴት በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ከቤተሰቧ ምሽግ ወጥታ “ነፃ ነኝ” ስትል፣ በምላሹ ያገኘችው ነገር ቢኖር የኑሮ ውድነትን፣ ማኅበራዊ ብቸኝነትንና በየደቂቃው የሚለዋወጥ የማኅበራዊ ሚዲያ ጫናን፣ ተጠቅሙውና አጥቅተው የሚጥሏት ለብቻ የመጋፈጥ ግዴታን ነው። ይህ ተፈጥሮአዊ ያልኾነ ጫና ደግሞ አእምሮን ለከፍተኛ መዛባትና መቅበዝበዝ ይዳርጋል።
የአባወራው ሚና መዳከም በቀጥታ የሚጎዳው በምሽጉ ጥላ ስር ሊጠበቁ የሚገባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው። አባወራው የምሽጉ ጠባቂ ኾኖ ሲቆም፣ በውስጡ ያሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና አዛውንቶች የሚተነፍሱበት የደኅንነት ቀጠና ይፈጠርላቸዋል።
ይህ መዋቅር ሲፈርስ ግን፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ለብቻው ዐለምን የሚጋፈጥ፣ ተዋጊ እንዲኾን ይገደዳል። በተለይም ሴቶች በምዕራባውያን ርዕዮተ-ዓለም ግፊት ተፈጥሮአዊና ባህላዊ ሚናቸውን “ዝቅተኛ” አድርገው እንዲቆጥሩትና በእርሱ ላይ እንዲያምጹ ተደርገዋል።
ይህ አመጽ ደግሞ በድል ሳይኾን በውድቀት ተጠናቋል። ምክንያቱም ሰው በማኅበራዊና ባህላዊ ዐውድ ውስጥ እንጂ ለብቻው በባዶ ቦታ ላይ ጤናማ ኾኖ ሊኖር አይችልም። የምሽጉ መፍረስ ያስከተለው መቅበዝበዝ፣ ሴቶችን ወደ ጭንቀት ክኒኖችና ወደ ዘላቂ ስሜታዊ መረጋጋት ማጣት መርቷቸዋል።
ዛሬ በከተማው ሰው ኑሮ ውስጥ የሚታየው “ተራማጅነት” ትውልዱን ከተፈጥሮአዊ መሠረቱ ነቅሎታል። ተራማጅ አስተሳሰብ ነባር እሴቶችንና የቤተሰብን ተዋረድ እንደ እንቅፋት ይቆጥራል።
ነገር ግን እነዚህ እሴቶች ለሰው ልጅ የሕይወት ትርጉምና ግብ የሚሰጡ ነበሩ። አንድ ሰው “የፈለግከውን መኾን ትችላለህ” በሚል የውሸት የተስፋ ቃል ምሽጉን ጥሎ ሲወጣ፣ የሚገጥመው ባዶነት ነው።
ይህ ባዶነት ደግሞ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ ወይም በጊዜያዊ መዝናኛዎች ሊሞላ አይችልም። ትውልዱ በመድኃኒት ላይ ጥገኛ መኾኑና ለጭንቀት መጋለጡ፣ በነፃነት ስም እራሱን ወደ ሱሰኝነት አዘቅት ከጣሉት ኬሚካሎች እስር ቤት ውስጥ እየቆለፈበት መኾኑን ያሳያል።
መቅበዝበዙ የሚመጣው ካረፉበትና ትርጉም ካገኙበት ስፍራ ተነቅለው፣ መቆሚያ በሌለው የርዕዮተ-ዓለም ጉዞ ውስጥ እንዲገቡ ስለተገደዱ ነው።
በመጨረሻም፣ ይህንን የተስፋፋ የአእምሮና የማኅበራዊ ቀውስ ለመግታት ብቸኛው መፍትሔ የፈረሰውን ምሽግ በድጋሚ መገንባት ነው።
🌟 ይህም ማለት የአባወራነትን ክብር መመለስ፣ የቤተሰብን ቅድስና ማጽናትና እያንዳንዱ አባል በምሽጉ ውስጥ ያለውን ትርጉም ያለው ሚና እንዲያውቅ ማድረግ ነው።
“መብት” እና “ነፃነት” ትርጉም የሚኖራቸው ከጥበቃና ከኃላፊነት ጋር ሲቆራኙ ብቻ ነው። ትውልዱ ከመቅበዝበዝ አርፎ ወደ ስክነት እንዲመለስ፣ ቀድሞ የፈረሰበትን የምሽግ እሴት ሊያስብና ወደዚያው ሊመለስ ይገባዋል።
ያለ ጠንካራ ቤተሰብና ያለ አባወራው መሪነት፣ ትውልዱ ለሥነ-ልቦናዊም ሆነ ለአካላዊ ጥቃት ተጋልጦ ከመቅበዝበዝ አይድንም። የምሽጉ መታደስ የሴቶች መከታ፣ የሕፃናት ተስፋና የአዛውንቶች መረጋጋት ዋስትና ነው።
ይህ ምሽግ ግን ለምን በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት ሰበብ ከቤተመንግሥት እስከ ቤተክህነት፣ ከትምህርት ቤት እስከ ግብረሰናይ ተቋማት ድረስ እንዲፈርስ ተዘመተበት?
ልጆቻችንስ ማስትሬትና ዶክትሬት እየሠሩ በእነዚህ እሴት በራዥ፣ ቤተሰብ አፍራሽ ተቋማት ውስጥ ዳጎስ ያለ ደመወዝ ተከፍሏቸው ትውልድን ለማጥፋት፣ ማኅበረሰብን ለማምከን ለምን መረጡ?
0 Comments