ሀገርን ለማፍረስ ዓላማ ላላት “እንዴት እንድትኖር” አይነግሯትም!


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

ቤተሰብ፡ የሰው ልጅ ሥልጣኔው የመጨረሻው ምሽግ፤ እርሱ ሲፈርስ የሰው ልጅም ሕልውና እንዲያከትም ከእኛ ይልቅ ጠላትና ሆዳደሩ ቅጥረኛው ያውቃሉ።

አንድን ማኅበረሰብ በጦር መሣሪያ ድል አድርጎ መግዛት ጊዜያዊ ድል ሊኾን ይችላል፤ ትውልድን ግን በቋሚነትና “በፈቃደኝነት”፣ በጉጉትም ባሪያ ለማድረግ መጀመሪያ በልቡናው ውስጥ የታነፁትን የመከላከያ አጥሮች(እሴቶች) ማፍረስ ግድ ይላል።

👉 በቋሚነት አልኩኝ፦ በዘላቂነት ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ እስከ ዘርማንዘሩ ባርያ ለማድረግ፤

👉 በፈቃደኝነት አልኩኝ፦ በኃይል፣ በጉልበት፣ በግዳጅ፣ ሳይኾን በውዳጅ እንዲመጣ፤

👉 በጉጉትም አልኩኝ፦ አስቀድመው ባርነቱን።፣ አንድም ወደ ባርነት የሚወስደውን መንገዱን አጽድቀውለት ግተውታልና፦እጠቀምበታለሁ ሲል ጓጉቶ፣ አንድም ከፍተኛውን ጥቅም አገኝበታለሁ ሲል ሽቶ፤ አንድም መንግሥተ ሰማያትን እወርስባታለሁ ሲል ተታልሎ አጥብቆ ተመኝቶ ይመጣል ስል ነው።

ለምሳሌ፦ ጃንደርብነትን “መንፈሳዊንት” ብለው አጽድቀውለት ልቡን እንዳጠፉበት ትውልዴ ያለ ነው።

እነዚህ የመከላከያ አጥሮች ደግሞ የሚገነቡት በመንግሥት ቢሮዎች፣ በቤተክርስስተያን ዐውደምኅረትም ኾነ በሰንበት ትምህርት ቤት ሳይኾን በቤተሰብ ውስጥ ነው።

🌟 ቤተሰብ የጥንታዊ እሴቶች፣ የሃይማኖት፣ የባህልና የሞራል መሠረቶች የሚጠበቁበትና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉበት ነባር፣ ጥንታዊ፣ መለኮታዊ፣ ኹነኛ፣ ልከኛ፣ መልካምና ውብ የኾነ ብቸኛና ጠንካራ ምሽግ ነው።

ዐዲሱንና ግብረ-ገብነት የሌለውን ዓለም አቀፋዊ ኅብረተሰብ ለመገንባት የሚሹ ኃይሎች፣ ይህንን ምሽግ ሳይንዱ ግባቸውን ማሳካት እንደማይችሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ።

ስለኾነም የቤተሰብ መዋቅርን ለማፍረስ “የሴቶች እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” የሚሉ እጅግ ማራኪና ሰብአዊ የሚመስሉ መፈክሮችን እንደ ስትራቴጂያዊ መሣሪያ ይጠቀማሉ።

በአሁኑ ወቅት በUN መሪነት የሚለቀቁት “ለሴቶች እንዴት እንደሚለብሱ፣ እንደሚናገሩና እንደሚኖሩ አትንገሯቸው” የሚሉ መፈክሮች በገጽታቸው የግለሰብ ነፃነትን የሚሰብኩ ቢመስሉም፣ ውስጠ-መልእክታቸው ግን የቤተሰብን የሥነ-ምግባር አቅጣጫ ጠቋሚነት፣ በተለይም የአባትን ይበልጡንም የአባወራውን ጠባቂነት”ጭቆና” አስመስሎ ማቅረብ ነው።

አንዲት ሴት በቤተሰቧ ውስጥ የምታገኘውን ምክርና ጥበቃ እንደ እስራት እንድትቆጥረው ሲደረግ፣ በቤተሰቡ ውስጥ ያለው የታማኝነት ክር፣ የፍቅሩም ሰንሰለት ይበጠሳል።

ይህ ክር ሲበጠስ ደግሞ ቤተሰቡ እንደ አንድ ወጥና ጠንካራ ተቋም የመቆም አቅሙ ይላላል። አባትን ወይም ባልን እንደ “አምባገነን”፣ እናትን ደግሞ እንደ “ተጨቋኝ” አድርጎ የሚፈርጅ ትርክት ሲሰፍን፣ በቤት ውስጥ ያለው ፍቅርና መከባበር በጥርጣሬና በፉክክር ይተካል።

አባወራነት በባህላችን ውስጥ የሥልጣን መቆናጠጫ ሳይኾን የኃላፊነትና የጥበቃ ማዕከል ነው። አንድ አባት በቤተሰቡ ውስጥ የሚሰጠው መመሪያና የሚያሳየው አርአያነት፣ ልጆቹ ነገ ለሀገራቸው ታማኝ፣ ሥርዓትን አከባሪና የማንነት ኩራት ያላቸው ዜጎች እንዲኾኑ መሠረት ይጥላል። ይህንን የአባወራነት ሚና “አምባገነንነት” ብሎ መፈረጅ፣ ዓላማው ቤተሰብን ያለ ጠባቂና ያለ መሪ ማስቀረት ነው።

ቤተሰብ መሪና ጠባቂ ሲያጣ ግለሰቡ ብቻውን ይቀራል፤ ብቻውን የቀረ ግለሰብ ደግሞ ለውጭ ተጽዕኖዎችና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች መመሪያዎች እጅግ ተጋላጭ ይኾናል።

በዚህ ሂደት ውስጥ “ነፃነት” እየተባለ የሚሰበከው ጽንሰ-ሀሳብ፣ ግለሰቡን ከቤተሰባዊ ጥበቃ አውጥቶ ለባዕዳን ርዕዮተ-ዓለሞች ባሪያ የማድረግ ስውር ስልት ነው።

ይህ ድርጊት በዘፈቀደ የሚሆን ሳይኾን የታቀደበት “የማኅበራዊ ምህንድስና” (Social Engineering) ውጤት ነው። ዓላማው ግለሰቦችን ከታሪካቸው፣ ከሃይማኖታቸውና ከባህላቸው ነቅሎ በማውጣት፣ ለማንኛውም ዐዲስ ፈጠራና ርዕዮተ-ዓለም አመቺ የኾኑ አድርጎ መፍጠር ነው።

ቤተሰብ ሲዳከም፦

👉 ልጆችን የማሳደግና የመቅረጽ ኃላፊነት ከወላጆች ወደ ማኅበራዊ ሚዲያና ወደ ባዕዳን ተቋማት፣ ትውልዱንም ለጠላት አሳልፈው ለሚሰጡት ሆዳደር ሊቃውንት ይሸጋገራል።

👉 የሀገር ኩራትና ብሔራዊ እሴቶች የሚተላለፉበት ሰንሰለት ይቋረጣል።

👉 ግለሰቦች ለቤተሰባቸውና ለሀገራቸው ሳይኾን ለዓለም አቀፋዊ (Globalist) የፍጆታ ሥርዓት ታማኝ ይኾናሉ።

ሀገር የምትቆመው በጡብና በሲሚንቶ፣ በአስፋልትና በሕንጻ ሳይኾን በጠንካራ ቤተሰብ መሠረትነት ላይ ነው።

ይህ “እንዴት ልትኖር እንዳላት አትንገራት” ማለት የመጣችበትን መሠረቷን፣ ሥሯን፣ ቤቷን፣ ሀገሯን ከምንምና ከማንም በላይ ደግሞ ራሷን እንድታጠፋ ልከናታል እንደማለት ነው።

እውነተኛው ነፃነት ከራስ ማንነትና ከቤተሰብ አጥር መውጣት ሳይኾን፣ በቤተሰብ ውስጥ ያለውን ፍቅር፣ መከባበርና የሥልጣን ተዋረድ ጠብቆ መቆየት ነው።

አባወራነትን ማጥቃት ሀገርን ማፍረስ መኾኑን ተረድተን፣ ይህንን የመጨረሻ ምሽጋችንን ከባዕዳን ርዕዮተ-ዓለም ወረራ ልንጠብቀው ይገባል።

አንድም ከቤተመንግሥት እስከ ቤተክህነት ከፍተኛ ጥቃት እየደረሰበት ላለው ምሽግ ቤተሰባችን፣ መሪና ጠባቂያችን ለኾነው አባወራዊ እሴታችን ዘብ ልናድር ይገባል።

የአባትም ኾነ የአባወራው ምክር “ጭቆና” አይደለም፣ ኾኖም አያውቅም፤ ምክር የጥበቃ አጥር እንጂ። አንድም የአባትም ኾነ የአባወራው ጥበቃ ሴቷን ከጥፋት “በደል” አይደለም፣ ኾኖም አያውቅም፤ የአባትና የአባወራው ጥበቃ ከጠላትና ከሆዳደሩ ቀማኛ የምትከተትበት ቅጥር እንጂ።


Post a Comment

0 Comments