በቀደሙት ክፍሎች የኔፍሊምን ታሪክ መሠረት እና በብሉይ ኪዳን የተጻፈውን ታሪካቸውን አይተናል።
ከመጽሐፈ ሄኖክም እጅግ በጥቂቱ ቃኝተናል። በዚህኛው ክፍል ደግሞ መጽሐፈ ሄኖክን በሰፊው እንዳስሳለን። ስለ ወደቁት መላእክት፣ ስለ ልጆቻቸው፣ በምድር ላይ ስለተከሰተው ኃጢአት፣ ስለመጣውም ቅጣት በሰፊው እንመለከታለን።
የተለያዩ ጸሐፊዎች መጽሐፈ ሄኖክን በተለያየ የምዕራፍ እና ቁጥር አቆጣጠር ነው የሚጽፉት። ነገር ግን እኛ በግዕዙ ብራና የሚገኘውን እና የዘርፉ ምሁራንም የሚስማሙበትን የምንጠቀም ይሆናል። በዚህኛው አከፋፈል፣ ምዕራፎቹ አጫጭር ሲሆኑ በቁጥርም 105 ናቸው። እነዚህም በአምስት መጻሕፍት የተከፈሉ ናቸው።
አሁን ለምናነሳው ርዕስ ደግሞ መረጃን የሚሰጡን ምዕራፎች፣ ከ6-14 እና ከ60-69 ያሉት ይሆናሉ። እነዚህን ሁሉ በአንድ ጽሑፍ መዳሰስ ስለማንችል ከላይ ከላይ ብቻ የተወሰኑ ጥቅሶችን የምናነሳ ይሆናል። በዋናነትም ከምዕራፍ 6-11 ያሉትን እንዳስሳለን።
ምዕራፍ 6
1. ወኮነ እምዘበዝሁ ውሉደ ሰብእ በእማንቱ መዋዕል ተወልዳ ሎሙ አዋልድ ሰናያት ወላህያት። 2. ወርእዩ ኪያሆን መላእክት ውሉደ ሰማያት ወፈተውዎን። ወይቤሉ በበይናቲሆሙ ንዑ ንኅረይ ለነ አንስተ እም ውሉደ ሰብእ ወንውለድ ለነ ውሉደ።
ትርጉም፦ በዚያም ወራት የሰው ልጆች በምድር ላይ በበዙ ጊዜ መልካም እና ውብ ልጆች ተወለዱላቸው። የሰማይ ልጆች የሆኑት መላእክትም እነሱን አይተው ተመኟቸው፣ እርስ በርሳቸውም፣ "ኑ ከሰው ልጆች መካከል ሴቶችን ለራሳችን እንምረጥ፣ ልጆችም እንውለድ" ተባባሉ።
እዚህ ጋ ወሳኝ ቃላት አሉ። "ኪያሆን"፣ "ወፈተውዎን"፣ "አንስተ"... እነዚህ ሁሉም የሴት ፆታን የሚያመለክቱ ናቸው። ኪያሆን ሲል በሶስተኛ ሰው የሴት ፆታ ላይ የሚደረግ ተግባርን ያመለክታል። ፈተውዎን ሲልም ተመኟቸው ወይም ፈለጓቸው ማለት ሲሆን "ን" የምትለዋ ቅጽል ተግባሩ በሴቶች ላይ የተደረገ መሆኑን ያመለክታል። መጽሐፈ ሄኖክ እጅግ በተደጋጋሚ ይህንን pattern ይጠቀማል። መላእክቱ ከሴቶች ጋር እንደተደመሩ እና ከነሱም ልጆች እንደወለዱ ነው የሚናገረው።
አንዳንዶች እንደሚሉት ደቂቀ ሴት ቢሆኑ ኖሮ እነሱ ወንዶችም ሴቶች ስላሉ ከላይ ያለው አንቀጽ በሴቶች ላይ ብቻ የተደረገ ሆኖ አይጻፍም ነበር። ማለትም ደቂቀ ሴት ሴቶቹን የቃየል ልጆች ብቻ ሳይሆን ወንዶቹንም ተመኟቸው ይባል ነበር። ስለዚህም ቃሉ "ኪያሆን" ሳይሆን "ኪያሆሙ" ይሆን ነበር።
ምዕራፍ ስድስት የቀረው ክፍል፣ ስምያዛ የተባባልነውን እንዳትክዱ ካላቸው በኋላ በኤርሞንኤም ተራራ ላይ መሃላ መግባታቸውን ይተርካል። ከዚያም ስማቸውን መዘርዘር ይጀምራል።
ምዕራፍ 6
7. ወዝንቱ አስማቲሆሙ ለመላእክቲሆሙ፦ ስምያዛ ዝንቱ ውእቱ መልአኮሙ። ኡራኪበራሚኤል፣ አኪበኤል፣ ጣሚኤል፣ ራሚኤል፣ ዳንኤል፣ ኤዜቄኤል፣ በራቁያል፣ አሳኤል፣ አርማሮስ፣ በጠርኤል...
8. እሉ እሙንቱ ሐበይቶሙ ለ፪፻ መላእክት በአሠርተ ወባዕዳን ኩሉ ምስሌሆሙ ወነስኡ ሎሙ አንስተ።
ትርጉም፦ የነዚህ መላእክት አለቆምች እነዚህ ናቸው ብሎ ስማቸውን ይዘረዝራል። እነዚህም አስሩ መላእክት የ200 መላእክት አለቆች ናቸው፣ እነሱም ተለያዩ እና ለየራሳቸው ሴቶችን ወሰዱ።
"መልአኮሙ" የሚለው ቃል በቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ የመላእክት አለቃን ለመግለጽ የምንጠቀምበት ነው። ለምሳሌ "ውእቱ ሊቆሙ ለመላእክት ወመልአኮሙ ስሙ ሚካኤል" ስንል ቅዱስ ሚካኤል የመላእክቱ አለቃ መሆኑን እየተናገርን ነው። ስለዚህ እነዚህም ወደ ምድር የወረዱት፣ በመላእክት ስርአት አለቆች አሉላቸው ማለት ነው።
እናም በተለይ ቀድሞ የተነሳው ስምያዛ ነው። እሱም፣ እናንተ ከካዳችሁኝ፣ ኃጢአቱ በኔ ላይ ይሆናል ብሏቸዋል። ይህም የሁሉም አለቃ እርሱ መሆኑን የሚያመላክት ይመስላል። በሌሎቹ የመጽሐፉ ክፍሎች ግን በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው እና አለቃም የሚመስለው አዛዝኤል ነው። ከላይ ያለው ዝርዝር ውስጥም አዛዝኤል የለም። ስለዚህ አዛዝኤል እና ስምያዛ አንድ ይሆኑ? በርግጥ ግልጽ መልስ የለም።
ሌላው ደግሞ ሳናነሳ ማለፍ የሌለብን፣ ከላይ ያለው አንድ ስም "ራሙኤል" ተብሎ ብዙ ጊዜ ይፃፋል። ይህም ብዙ ሰዎች ዘንድ ትልቅ ጥርጣሬን እና ምቾት ማጣትን ይፈጥራል። ምክንያቱም ራሙኤል ከቅዱሳን መላእክት አንዱ ነው። ስለዚህ እንዴት ከወደቁት መላእክት ዘንድ ሊጠቀስ ቻለ? መልሱን የምናገኘው የግዕዙን ብራና በጥንቃቄ ስናነብ ነው። የተጠቀሰው ስም "ራሙኤል" ሳይሆን "ራሚኤል" ነው። ስለዚህ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው፣ አንዱ (ራሚኤል) የወደቀ መላእክት፣ አንዱ ደግሞ (ራሙኤል) ዛሬም ከቅዱሳን መላክት ዘንድ የሚጠቀስ ነው ማለት ነው።
እንቀጥል።
ምዕራፍ 7
1. ወነሥኡ ሎሙ አንስት ወኀረየ ኩሉ ለለ ርዕሱ አሐተ አሐተ። ወወጠኑ ይባኡ ኀቤሆን ወተደመሩ ምስሌሆን ወመህርዎን ሥራያተ። ወስብዐአታተ ወመቲረ ሥርው ወዕፅው ወአመርዎን።
2. ከእማንቱሰ ፀንሳ ወወለዳ ረዓይተ ዐበይተ ወቆሞሙ በበ፫፻ በእመት።
ትርጉም፦ ለራሳቸውም ሴቶችን ወሰዱ እያንዳንዱም አንድ አንድ ለራሱ መረጠ። እነሱ ዘንድ መግባትም ጀመሩ አብረዋቸውም ተደመሩ አስማት/ምትሃት እና ስር መበጠስን እፅዋትን አስተማሯቸው አሳወቋቸው። እሱም ፀነሱና ትላልቅ ግዙፋንን ወለዱ ቁመታቸውም 300 300 ክንድ ነበር።
እዚህም ጋር የግዕዝ ቋንቋ በደምብ ፆታን ለይቶ አስቀምጧል። "ኀረየ አሐተ" ሲል አሐተ አንድ ቁጥር ለሴት ነው። "ባኡ ኀቤሆን" ሲል ወደነሱ ገቡ። "ኀቤሆን" ወደ እነሱ እነሱም ሴቶች ናቸው። "እማንቱሰ ፀንሳ ወወለዳ" ሲል የፀነሱትና የወለዱት ሴቶች ናቸው። እናም መላእክቱ አስማትና ምትሃት ያስተማሩት ለነዚያ ሴቶች ነው። ስለዚህም ከዚያ በኋላ የሴት አስማተኞች ተፈጠሩ ማለት ነው።
እንቀጥል።
ምዕራፍ 7
3. እሉ በልኡ ኩሎ ፃማ ሰብእ እስከ ስእንዎን ሴስዮተ ሰብእ።
4. ወተመይጡ ረዓይት ላእሌሆሙ ይብልዕዎሙ ለሰብእ።
ትርጉም፦ እነሱም የሰውን ምግብ ሁሉ በሉ አልበቃም ሲላቸው ሰዎችን ወደ መብላት ተመለሱ።
ከዚህ ቀጥሎም በወፎች በእንስሳት በአሳዎች ሁሉ ላይ ኃጢአት ሰሩ፣ እርስ በርሳቸውም ተበላሉ፣ ምድርም የነሱን አመፃ አልቻለችም ይለናል። ምናልባት የሰውን ስጋ መብላት የተጀመረው በዚህ ጊዜ ይሆን? የሰው ስጋ የሚበሉ የተፈጠሩት በዚህ ምክንያት ይሆን?
ምዕራፍ 8
1. ወአዛዝኤል መሀሮሙ ለሰብእ ገቢረ አስይፍት ወመጥብኀት ወወልታ ወድርአ እንግድዓ አርአዮሙ ወምግባሮሙ እምድኅሬሆሙ። ወአውቃፋተ ወሰርጐ ወተኩሕሎተ ወአሰንዮ ቀራንብት ወእብን እምኩሉ እብን ክቡር፤ ወኅሩየ ወኩሎ ጥምዓታተ ኅብር ወተዋለጠ ዓለም።
ትርጉም፦ አዛዝኤልም የሰይፍና የጦርን፣ የተለያዩ የደረትና የሌሎችም መከላከያዎች (armors) እና እንዴት እንደሚሰሩ አስተማራቸው። እንዲሁም ጌጣጌጦችን፣ ኩል መኳልን ቅንድብ ማሳመርን፣ የተለያዩ ክቡር ድንጋዮችን፣ የተለያዩ ቀለማ ቀለሞችንም አስተማራቸው።
2. ወኮነ ርስዓን ዐቢይ ወብዙኅ። ወዘምዎ ወስሕቱ ወማሰነ ኩሎ ፍናዊሆሙ።
ትርጉም፦ ከዚያም ታላቅና ብዙ ክፋት በደል ተከናወነ። ዝሙትን ዘሞቱ፣ ሳቱ፣ መንገዳቸው ሁሉ ተበላሸ ወይም ረከሰ።
ከዚህም ቀጥሎ ሌሎቹ መላእክት ምን ምን እንዳስተማሯቸው ይዘረዝራል። የተለያዩ አስማትን ኮከብ ቆጠራን ቅጠል መበጠስን ወዘተ አስተማሯቸው። በሰሩት ግፍም የሰዎች ጩኸት ወደ ሰማይ ደረሰ። ማለትም ብዙ ንፀሃን ሰዎችን ገደሉ ብዙ ግፍ እና ዐመፃን አደረጉ።
ምዕራፍ 9
1. ወአሜሃ ኀወጹ ሚካኤል ወኡርኤል ወገብርኤል እምሰማይ ወርእዩ ብዙኅ ደም ዘይትከዐው በዲበ ምድር ታሕተ ወኩሎ ዘይትገበር ዐመፃ በዲበ ምድር።
2. ወይቤሉ በበይናቲሆሙ ቃለ ጽርኃቲሆሙ ዕራቃ ጸርኀት ምድር እስከ አንቀጸ ሰማይ። 3. ወይእዜኒ ለክሙ ቅዱሳነ ምድር ይሰክዩ ነፍሳተ ሰብእ እንዘ ይብሉ ኀበ ልዑል አብኡ ለነ ፍትሐ።
ትርጉም፦ ያን ጊዜም ሚካኤል፣ ኡራኤል እና ገብርኤል ከሰማይ ሆነው ምድርን ሲመለከቱ በምድር ላይ የሚደረገውን ዓመፃ እና የሚፈሰውን ደም አዩ። እንዲህም ተባባሉ ምድር ተጣራች ድምጿ እስከ ሰማይ። አለችም "እናንተ የሰማይ ቅዱሳን የሰዎች ነፍሳት ይጣራሉ ከልዑል ዘንድ ፍትህን አምጡልን እያሉ"
3. ወይቤሉ ለእግዚኦሙ ለንጉስ እስመ እግዚኦሙ ለአጋእዝት ወአምላኮሙ ለአማልክት ወንጉሦሙ ለነገሥት። ወመንበረ ስብሐቲሁ ውስተ ኩሎ ትውልደ ዓለም ወቡሩክ ወስቡሕ።
4. አንተ ገበርከ ኩሉ ወስልጣነ ኩሉ ምስሌከ ወኩሉ ክሱት ቅድሜከ ወግሁድ ወአንተ ትሬኢ ኩሎ ወአልቦ ዘይትከሃል ይትኃባእ እምኔከ።
ትርጉም፦ ቅዱሳን መላእክቱም ለእግዚአብሔር አሉት "አንተ የጌቶች ጌታ የአማልክት አምላክ የነገስታት ንጉስ ነህ የምስጋናህ መንበር በሁሉ ትውልድ ዘንድ ነው የተባረከና የተመሰነገም ነው። አንተ ሁሉን ፈጠርክ የሁሉም ሰልጣን ባንተ ዘንድ ነው ሁሉም ነገር ባንተ ዘንድ ግልጥ ብሎ የሚታይና ገሃድ የሆነ ነው ካንተ መደበቅ የሚችልም የለም።
5. ርኢከ ዘገብረ አዛዝኤል ዘከመ መሀረ ኩሎ ዐመፃ በዲበ ምድር ወአግሀደ ኅቡዓተ ዓለም እለ ይትገበራ በሰማያት። 6. ወአመረ ስብዐታተ ስምያዛ ዘአንተ ወሀብኮ ስልጣነ ይኰንን እለ ምስሌሁ ኅቡረ
ትርጉም፦ አዛዝኤል ያደረገውን፣ በምድር ላይ ዐመፃን ሁሉ እንዳስተማረ በሰማያት የሚደረጉ ድብቅ/ስውር ምስጢራትንም እንደገለጠ አየህ። ስምያዛም አንተ አብረውት ያሉትን እንዲፈርድ የሰጠኸውን ስልጣን አልተጠቀመም።
ከዚህ ቀጥሎም ወደ ሴቶቹ ገብተው ኔፍሊምን(ረዓይትን) እንደወለዱና ግፍም እንደበዛ የሰዎች ነፍሳትም ወደ ሰማይ እንደጮሁ ይናገራሉ -- ቅዱሳን መላእክቱ።
እዚህ ጋር አንድ የምናስተውለው ነገር፣ አዛዝኤል የገለጣቸው ነገሮች አንዳንዶቹ በሰማያት በመላእክት ዘንድ የሚደረጉ፣ ለሰዎች ግን የተከለከሉ ናቸው። ይህም ለምን ብንል ሰዎች ስለሚስቱ ስለሚወድቁ ነው። ይህንንም እዚሁ ጋር በተግባር አይተናል። መላእክት ከሰዎች ከፍ ያለ እውቀት፣ ነገሮችን የመረዳት ችሎታ እና መንፈሳዊ ኃይል አላቸው። ስለዚህ የሚይዙት ሰይፍ እና የጦር መሳርያ እንዲሁ ያገኙትን እንዲገድሉበት አያደርጋቸውም። የከዋክብትን አካሄድ ማወቃቸውም ወደ ጥንቆላ አይወስዳቸውም። የሰው ልጆች ግን ደካማ ስለሆኑ በዚያ ወደቁ። ከመላእክቱ እና ከሰው የተወለዱት ኔፍሊምም እንዲሁ ወደቁ። እንዲያውም ጨካኝ እና ነፍሰ ገዳይ ሆነው የንፁሐንን ደም አፈሰሱ፣ ያ ደምም ወደ ሰማይ ተጣራ።
ቀጣዩ ምዕራፍም የእግዚአብሔርን ምላሽ ያሳየናል።
ምዕራፍ 10
1. ወአሜሃ ልዑል ዓቢይ ወቅዱስ ተናገረ። ወፈነዎ ለአርስየላልዩር ኀበ ወልደ ላሜክ። ወይቤሎ
2. በሎ በስመ ዚአየ ኅባዕ ርዕስከ። ወአግህድ ሎቱ ፍጻሜ ዘይመጽእ እስመ ትትሐጎል ኩላ ምድር ወማየ አይኅ ይመጽእ ሀሎ ዲበ ኩላ ምድር ወይትኀጎል ወሀሎ ውስቴታ።
3. ወይእዜኒ መሀሮ ከመ ይንፈጽ ወይንበር ዘርኡ ለኩሎሙ ትውልድ።
4. ወይቤ ካዕበ እግዚእ ለሩፋኤል እስሮ ለአዛዝኤል በእዴሁ ወእግሩ ወደዮ ውስተ ጽልመት። ወአብቅዋ በገዳም እንተ ሀለወት በዱዳኤል ወደዮ ህየ።
5. ወደይ ላዕሌሁ አዕባነ ጠዋያተ ወበሊሐተ ወክድኖ ጽልመተ። ወህየ ይኅድር ወክድኖ ለገጹ ከመ ኢይርአይ ብርሃነ።
6. ወበዕለት ዐባይ እንተ ኩነኔ ከመ ይትፈነው ውስተ ዋእይ።
ትርጉም፦ ያን ጊዜም ታላቅና ቅዱስ የሆነው ልዑል ተናገረ "አርስየላልዩር" የተባለውንም (መልአክ) ወደ ላሜህ ልጅ (ኖህ ማለት ነው) ላከ። መልአኩንም አለው፦
በኔ ስም ራስህን ደብቅ የሚመጣውንም ፍጻሜ ግለጥለት ምድርም እንደምትጠፋ የጥፋት ውሃም በምድር ላይ እንደሚመጣ በውስጧም ያለው እንደሚጠፋ አሳውቀው። ዳግመኛም እግዚአብሔር ለሩፋኤል አለው፦ አዛዝኤል እጅና እግሩን እሰረው በጨለማም ጣለው። ዱዳኤል በሚባለው ስፍራ ባለ በረሃም ጣለው። በላዩ ላይም የተሳሉ ድንጋዮችን ጨምርበት ብርሃን እንዳያይም/እንዳያገኝም ዝጋበት። እስከ ዓለም ፍጻሜም በዚያ ይኖራል በታላቋ የፍርድ ቀንም ወደ እሳት ይጨመራል።
ስለዚህ እግዚአብሔር አንዱን መልአክ ወደ ኖህ ልኮ ስለ ጥፋት ውሃ ነገረው። አንዱን ደግሞ አዛዝኤልን በጭለማ ውስጥ እንዲያስር ላከው። እስከ ዓለም ፍጻሜም ታስሮ ይቆያል።
ምናልባትም የሚስጥር ማህበራት ሁሌ ስለ ዓለም ፍፃሜ የሚያወሩት በዚያ አመካኝተው እርሱንና ጓደኞቹን ሊፈቱ ፈልገው ይሆን? ያ ግን በነሱ ስልጣን አይቻልም።
በተጨማሪም አዛዝኤል የታሰረው በሲኦል እንዳልሆነ ልብ በሉ። በምድር ላይ፣ በረሃ ባለበት አከባቢ ታስሮ በድንጋይ ነው የተዘጋበት። "ደቂቀ ሴት" ማለትም የአዳም ልጅ የሴት ልጅ ሙሉ ሰው ቢሆን በቀጥታ ሲኦል አልነበር የሚገባው? ነገር ግን ይህ መልአክ ስለሆነ የተለየ ቅጣት ተሰጠው።
9. ወለገብርኤል ይቤሎ እግዚአ፣ ሖር ዲቤሆሙ ለመንዝራን ወለምኑናን ወዲበ ውሉደ ዘማ።
ወአሕጉሎሙ ውሉደሙሂ ወለውሉደ ትጉሃን እምሰብእ ወአውፅኦሙ ወፈንዎሙ በበ በይናቲሆሙ እሙንቱ ወለሊሆሙ በቀትል ይትኀገሉ እስመ ኑኀ መዋዕል አልቦሙ። 10. ወኩሎ ይስእሉከ ወኢይኩን ለአበዊሆሙ በእንቲአሆሙ እስመ ይሴፈው ይሕየው ሕይወተ ዘለዓለም ወከመ ይሕየው ፩ ፩ እምኔሆሙ ፭፻ ክራማተ።
ትርጉም፦ ጌታም ለገብርኤል አለው፦ ሂድ ወደ አመንዛሪዎቹ እና ስፍራቸውን ወደ ተዉት፣ ወደ ዘማውያኑም ልጆች፤ ልጆቻቸውንም የትጉሃን ልጆችን አጥፋቸው። ወደ አንድ ቦታ አውጣቸው እና በቡዱን በቡድን አድርገህ በጦርነት እንደጠፋፉ አድርጋቸው ኑኀ ዘመን (ረጅም እድሜ) እንዳይኖራቸው። የዚያን ጊዜም አባቶቻቸው (የኔፍሊም አባቶች) ይህንን ሲያዩ ይለምኑሃል፣ እንደ ልመናቸው እንዳይሆን አትስማቸው። ልጆቻቸው የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖራቸው፣ እያንዳንዳቸው 500 500 ዓመት እንዲኖሩ ተስፋ ያደርጋሉና።
11. ወለሚካኤል ይቤሎ እግዚአ፤ ሖር አይድዕ ለስምያዛ ወለካልኣን እለ ምስሌሆሙ እለ ኀብሩ ምስለ አንስት ከመ ይማስኑ ምስሌሆን በኩሉ ርኩሰ ዚአሆን።
12. ወሶበ ይትራገዙ ኩሉ ውሉዶሙ ወሶበ ይሬእዩ ኩሉ ሐጉሎሙ ለፍቁራኒሆሙ እስሮሙ ለሰብአ ትውልድ በመትሕተ አውግረ ምድር እስከ ዕለተ ኩነኔሆሙ።
ወተፍጻሜቶሙ እስከ ይትፈጸም ኩነኔ ዘለዓለመ ዓለም።
13. ወበውእቱ መዋዕል ይወስድዎሙ ውስተ መትሕተ እሳት። በፃዕር ወበቤተ ሞቅሕ ይትዐጸው ለዓለም።
14. ወሶበ ይውኢ ወይማስን እምይእዜ ምስሌሆሙ ኅቡረ ይትኀአሰሩ እስከ ተፍጻሜተ ትውልድ።
ትርጉም፦ ጌታ ለሚካኤልም አለው፦ ሂድ ለስምያዛ እና ሁለተኛዎቹም አብረዋቸው ከሴቶች ጋር ለረከሱት አጠፋፋቸውን አሳውቃቸው/ንገራቸው። ልጆቻቸውም ሲወጋጉ (ሲገዳደሉ) በሚመለከቱ ጊዜ፣ የሚወዷቸው ሲጠፉ በሚያዩ ጊዜ እነሱንም ወስደህ ከምድር መሠረቶች በታች እሰራቸው እስከ ፍርዳቸው ቀንም ይቆያሉ። በዚያም ቀን ከእሳት በታች ይወስዷቸዋል በትልቅ ስቃይም በሚያቃጥል ቤት/ስፍራ ለዘላለም ይኖራሉ። እሳቱም እያቃጠላቸውና አካላቸውን እያበላሻቸው እስከ ትውልድ ሁሉ ፍጻሜ ድረስ ይታሰራሉ።
ከዚህም በኋላ ይህ ምዕራፍ፣ የወደቁት መላእክት እና ኔፍሊም ልጆቻቸው በምድር ላይ ስለሰሩት ግፍ ምክንያት እንደተቀጡ፣ እነሱ ከጠፉ በኋላ ምድር እንደምትታደስና እንደ አዲስም ጽድቅ እና እውነት ፍትህም እንደሚመለሱ ምድርም አዲስ እጽዋትን እንደምታበቅል ይተርካል።
ቀጣዩ ምዕራፍ ደግሞ የሚተርክልን፦ ጻድቁ ሄኖክ እነ አዛዝኤል ፊት ቀርቦ ይቅርታ እንደማይገኝላቸው ይነግራቸዋል። መላእክቱም ሄኖክን በእግዚአብሔር ፊት እንዲለምንላቸው ወይም እንዲያማልዳቸው ይጠይቁታል እርሱም ያንን ልመናቸውን ምልጃቸውን ጽፎ በእግዚአብሔር ፊት ያቀርባል። እግዚአብሔርም ለነሱ ይቅርታ እንደማይደረግ ይናገራል። በዚያም ምክንያት በሰሩት ሃጢአት ስለ አፈሩ ወደሰማይ ቀና ብለው አያዩም፣ አፍረው ዝም ይላሉ።
በኋላ ላይ በምዕራፍ 60፣65 እና 69 ይህ ታሪክ በድጋሚ ተብራርቶ እናገኘዋለን። ቀድሞ ያልተጠቀሱ መላእክት ስማቸው ተጠቅሶ እና ያስተማሩት ትምህርትም ተዘርዝሮ ተጠቅሷል። እንዲሁም የጥፋት ውሃው ከመምጣቱ በፊት ኖህ ጸሎት አድርጎ ሄኖክን እንደጠራው፣ ሄኖክን አግኝቶት እንዳረጋጋው እና እንደ አጽናናው ማየት ይቻላል። ይህንንም ግልጽ ለማድረግ ያህል። ይህ የጥፋት ውሃ የሚከሰተው ሄኖክ 500 ዓመት ሲሆነው ነው። ነገር ግን ሄኖክ በ365 ዓመቱ ተሰውሮ ነበር። ማለትም ሞትን ሳያይ ወደ ብሔረ ሕያዋን ተወስዶ በዚያ ነበር። እናም ኖህ ወደ ሄኖክ ጸልዮ የጠራው በዚያ ምክንያት ነው።
0 Comments