ቤተክርስቲያን፡ "Holistic" የኾነ ሕክምና የምትሰጥበት የራሷ ሆስፒታሎችና የሕክምና ኺደት ፕሮቶኮሎች ሊኖሯት ይገባል

✍ መስከረም ለቺሳ (ዶ/ር) | ዮቶጵያ

ከደም ልገሳ እና ከመንፈሳዊነት ጋር ተያይዞ፡ በመወያያ ቡድኑ እየቀረቡ ያሉ መረጃዎች ግሩም ናቸው። 

እኔ በበኩሌ፡ ቤተክርስቲያን፡ "Holistic" የኾነ ሕክምና የምትሰጥበት የራሷ ሆስፒታሎችና የሕክምና ኺደት ፕሮቶኮሎች ሊኖሯት ይገባል ባይ ነኝ።

ባጋጣሚ አክስቴን ሳስታምም፡ አንዲት ድንገት ገብታ የሞተች አራስ እያየሁ ነበር። ሁኔታዋ ለቤተሰቦቿ ኹሉ ድንገተኛ ስለኾነባቸው፡ ድንጋጤያቸውና ጩኸታቸው እጅግ ያሳዝን ነበር። ደኅና የነበረች ልጅ ናት፡ ድንገት ከአራስ ቤት እየጮኸች መጥታ የሞተችው። የኾነ መንፈስ የመታት ትመስላለች እንጂ፡ ይኼ ነው የሚባል ግልጽ ችግር ያገኙላት አይመስለኝም። 

እንዲህ ያሉ ነገሮች ብዙ ጊዜ ይፈጠራሉ። የተሻለ ሕክምና ክርስቲያኖችም ኾኑ በጥቅሉ የሰው ልጆች የሚያገኙበት መንገድ መኖር አለበት። አንድ ሰው ማናቸውም ጉዳት ሲደርስበት፡ አስታማሚዎቹ "ጸበል እንውሰደው? ወይስ ባሕላዊ ባለመድኃኒት ጋር ይኺድ? ወይስ ሆስፒታል እንውሰደው?...."  ብለው ግራ መጋባት የለባቸውም። ከሥጋዊ ሐኪም ጋር አብረው መንፈሳዊ ሐኪምና ባሕላዊ ሐኪም እዚያው አንድ ሆስፒታል ውስጥ መገኘት አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ጸሎት ለሚያስፈልገው ሰው፡ ግሉኮስ ብቻውን መፍትሔ አይሰጥም። ኦክስጂን ያጠረውን ሰው፡ ጸበል ለመውሰድ ጉዞ መጀመር ስኅተት ይፈጥራል። ምግብ በማጣት ስኳሩ ወርዶ ለወደቀ ሰው፡ የመድኃኒት ብዛት ነፍሱን አያተርፈውም። ሰው የሥጋ፣ የነፍስና የመንፈስ ውሕደት ነው። ሥጋውን ብቻ ማከም መፍትሔ አይሰጥም። ኹሉም ሕክምና በአንድ ቦታ መኖር አለበት። 

ከዚያም አልፎ፡ መንፈሳዊ ድንበሮችን ያልተላለፉ የሕክምና አሰጣጦችን ያከበረ ሕክምና ክርስቲያኖች ሊኖራቸው ይገባል። እውን የቆረበ ሰው፡ ካልቆረበ ሰው ደም መቀበል ይችላል? አንድ ሐኪም፡ አስቀድሞ ሳይጸልይ ቀዶ ጥገና ማድረግ አለበት? በዓይን የማይታዩ በሽታ አምጪ መናፍስትን፡ disinfect በማድረግ ብቻ ማጥፋት ይቻላል? ካህናትና መነኮሳት የሚታከሙበት መንገድ፡ አንዳንድ ነገሮች ላይ፡ ከምዕመናን ጋር ተመሳሳይ ነው? ....ብዙ ነገር አለ። መቼም መንፈሳዊውም፥ ሥጋዊውም እውቀት ያላቸው ሐኪሞች ብዙ ነገር ሊሉን እንደሚችሉ እገምታለሁ። 

ይኽን የሕክምና ፕሮቶኮል ወይም ኤቲክስ፡ የዓለም የጤና ድርጅት አይደለም የሚቀርጽልን፤ የኛው ኃላፊነት ነው።

ያው... ለወደፊት.... ልብ ስንገዛ ማለቴ ነው።

ባሁኑ አያያዝ ግን፡ አስተካክሎ መርፌ የሚወጋ ሐኪምም ማግኘት ትልቅ ነገር ነው።


Post a Comment

0 Comments