ድብቁ የኔፍሊም ታሪክ፣ ክፍል 4፦ የወደቁት መላእክት ያስተማሩት ትምህርት

✍ እለ አጽበሐ | አዲስ ምልከታ

በዚህ ክፍል፣ የወደቁት መላእክት ለሰዎች ያስተማሯቸውን ትምህርቶች እንመለከታለን።

መላእክቱ ለሰዎች ያስተማሯቸው መጥፎ እውቀቶች ብዙ ናቸው። እነዚህም የሰውን ልጆች ለብዙ ስህተት እና ጥፋት የዳረጉ ናቸው። ነገር ግን እነዚህ እውቀቶች አንዳንዴ እንደ ባለ-ሁለት ስለት ሰይፍ ሊታዩ ይችላሉ። በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ጠላትን ስለሚቆርጥ ለባለቤቱ ይጠቅማል። ነገር ግን ወደ ኋላ ከተመለሰ ባለቤቱንም ስለሚቆርጠው ይጎዳል።

ታዲያ እነዚህ መላእክቱ ያስተማሯቸው እውቀቶች አንዳንዶቹ እንዲህ ናቸው። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ጎጂ የሆኑም ነበሩ። ያንን ለመለየት እስኪ በመጀመሪያ እነዚህን እውቀቶች እንዘርዝር። የወደቁት መላእክት አስተማሯቸው የተባሉት ትምህርቶች እነዚህ ናቸው።

- የጦር መሳርያ አሰራር
- ጌጣጌጥ እና ኮስሞቲክስ (ኩል፣ የሚቀቡ ቀለሞች)
- የተለያዩ ደንጋዮች እና ክቡር ድንጋዮች (ዕንቁዎቹ)
- ኮከብ ቆጠራ
- ስር መቁረጥ
- በእንስሳት ላይ የተሰራ ስራ (በደምብ ያልተገለጸ)

እነዚህ ነገሮች ሁላቸውም በአጭሩ የተገለጹ ናቸው። ስለዚህ እስኪ አንድ በአንድ እንመልከታቸው።

በመጀመሪያ፣ የጦር መሳርያ እና ድንጋዮች የሚለውን አንድ ላይ እንይ። የጦር መሳርያ ለመስራት ብረታ ብረት ያስፈልጋል። እንደ መዳብ፣ አይረን፣ ነሃስ ያሉ ብረቶች ያስፈልጋሉ። እነዚህም የሚመጡት ከመሬት ውስጥ መአድን በማውጣት ነው። ከዚያም የተለያዩ የማቅለጥ እና ልሎችም ሂደቶች ውስጥ አልፎ ብረቱ ከመአድኑ ይለያል። ከዚያም ብረቶችን በመቀላቀልም እንደ ነሃስ አይነት የብረት ቅልቅሎች ይፈጠራሉ። ከዚያም የተለያዩ የጦር መሳርያዎች ይሰራሉ። ስለዚህ መጽሐፈ ሄኖክ "ድንጋዮች" ሲለን ስለ ዕንቁዎች ብቻ አይደለም፣ መእድን ስለሚገኝባቸው አለቶችም ጭምር እንጂ። ስለዚህ የወደቁት መላእክት መአድን ማውጣትን ለሰው ልጆች አስተምረዋል ማለት ነው።

ከዚያ ደግሞ የከበሩ ድንጋዮች ወይም ዕንቁዎች አሉ። እነዚህ በራሳቸው ክፋት የላቸውም። ለክፉም ለመልካምም መጠቀም ይቻላል። ለምሳሌ ብዙ የማይታወቀው በኛ ዘመን የጠፋው "ናብሊስ" የተሰኘ ዕንቁ አለ። ይህ እንቁ ሲመቱት የራሱን ድንጽ ያወጣል። ያም ድምጽ የታመመ ሰው ከሰማው ህመሙ ይሻለዋል። ይህም ዕንቁ አዳም ይጠቀምበት እንደነበር የሚያመላክቱ እንደ መልክአ ማርያም መጻሕፍት አሉ።
ከነዚህም ዕንቁዎች ብናይ፦ ጳዝዮን (Topaz)፣ ሰንፔር (Sapphire)፣ ኢያስጴድ (Jasper)፣ አሜቴስጢኖስ (Amethyst)፣ ዕንቁ-ባሕርይ (Pearl)፣ ሩቢ(Ruby)፣ ክርቲሎቤ (Chrysolite) ወዘተ ይገኙበታል። የየራሳቸው ልዩ ቀለምም አላቸው። ለምሳሌ ሩቢ ደማቅ ቀይ ነው፤ ዕንቁ ባሕርይ ንጹሕ ነጭ ነው፤ አሜቴስጢኖስ ወይን-ጠጅ ቀለም ነው፤ ክርቲሎቤ ደግሞ አረንጓዴ ነው።

ዕንቁዎች


እነዚህ ክቡር ድንጋዮች በተለያየ መልኩ ይገለጻሉ። ለምሳሌ እነዚህን 12 ጠቅሶ በአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ምሳሌ የሚጠቅስ ትምህርት አለ። የጳዝዮን ዕንቁም ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል። ሄኖክም የስላሴ መንበር ፊት በቀረበ ጊዜ ስፍራው በእብነ በረድ እና በሰንፔር (Sapphire) ዕንቁ ያጌጠ መሆኑን ይጠቀሳል።

በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህ ዕንቁዎች ለመጥፎ ጥቅም ይውላሉ። ከጥንቆላ እና መሰል ነገሮች ጋር የተያያዘ ጥቅም አላቸው። ለነዚህ ጥቅም የሚፈልጉ ሰዎችም በቤታቸው በማስቀመጥ፣ በጣታቸው ቀለበት በማሰራት ወዘተ ይጠቀሟቸዋል። ታዲያ በመጽሐፈ ሄኖክ የተጠቀሰው፣ የወደቁት መላእክት ያስተማሩት የተከለከለ እውቀትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ለመጥፎ ተግባር ዕንቁዎቹን የመጠቀም ይሆናል።
ሌላው መላእክቱ ያስተማሩት ደግሞ ጌጣጌጥ እና መዋብያዎች ነው። ታዲያ መጽሐፈ ሄኖክ ስለ እነዚህ የመዋቢያ ነገሮች ከጠቀሰ በኋላ ወድያው፣ "ሁሉም ሳቱ፣ ዝሙትን ፈጸሙ" ይለናል። ይህም የሚያሳየን ጌጣጌጦች እና እንደ ኩል ወዘተ ያሉት፣ ዛሬ "ኮስሞቲክስ" የምንላቸው፣ የመጨረሻ ውጤታቸው የሰው ልጆችን በዝሙት እንዲወድቁ ማድረግ ነው። ነገር ግን፣ ያም ሆኖ ሳለ ሰዎች በኛም ዘመን ለበዓላት እና ለሰርግ ለመሳሰሉት ጊዜያት ይጠቀሟቸዋል።

የኮከቦች ነገርም መላእክቱ ያስተማሩት ሌላ እውቀት ነው። ይህ ግን ሰፋ ያለ ነገር ነው። ለሰው ልጆችም ያስማሩት የተለያዩ መላእክት ናቸው። አዛዝኤል ይህንን አስተማረ፣ ይህኛው መልአክ ደግሞ ይህንን አስተማረ እያለ ሲዘረዝር፣ የኮከቦችን ነገር ግን ሁለት እና ሶስት መላእክት ናቸው ያስተማሩት። ይህ ለምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅስ?

ያንን ስንጠይቅ መልስ እናገኛለን። በመጀመሪያ የመላእክት ነገር፣ በሰማይ ላይ የሚዞሩ እና ኡደት (cycle) ያላቸው ናቸው። ማለትም ሰማይን ሁሌ ይዞራሉ፣ መዞራቸውም ሁሌም አይቆምም። ይህም የከዋክብት፣ የፀሐይ እና ጨረቃ ኡደት የሰው ልጅ ጊዜን እና ዘመንን ለመቁጠር የሚጠቀምበት መንገድ ነው። የዘመን አቆጣጠር በፀሐይ፣ በጨረቃ እና በከዋክብት መከናወን ይችላል። ለዚያ ነው የተለያዩ የፀሐይ እና የጨረቃ ካላንደሮች ያሉት። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ካላንደር የፀሐይ ካላንደር ነው። የአረቦች እና የቻይኖች ደግሞ የጨረቃ ካላንደር ነው። ታዲያ የካላንደር አሰራር እጅግ የተወሳሰበ እና ከፍተኛ የማሰብ፣ የማስተዋል አቅምን የሚጠይቅ ነው።

ይህ ስርአት ከካላንደርም አልፎ የወቅቶችን ሁኔታ ይወስናል። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ሄኖክ የጻፈውን (የወደቁት መላክእት አስተምረውት ሳይሆን ቅዱሳን መላእክት እያዘሩ አሳይተውት) የከዋክብት፣ የፀሐይና የጨረቃ ስርአትን ተጠቅማ ነው ካላንደርን እና የወቅቶችን ስርአት የሰራችው።
የኮከቦች ነገር ከዚህም ያልፋል። በመላው የዓለም ታሪክ፣ ባሕረኞች መንገዳቸውን የሚያውቁት ኮከቦችን ተጠቅመው ነበር። በጣም ለረጅም ዘመን ኮምፓስ አልነበረም፣ ጀልባቸውም በሌሊት በውሃ መካከል ይሄዳል። ስለዚህ መንገድ ላለመጥፋት ወሳኙ መንገድ ከዋክብትን መከታተል ነው።

ከዚህ በተረፈ ግን ከዋክብትን ተጠቅሞ ጥንቆላ የመስራት፣ የሰውን እጣ ፈንታ፣ ማንነት ለማወቅ የመፈለግ ነገር አለ። ይህ ነው መጥፎው ነገር። የወደቁት መላእክት የሰሩት አንዱ ጥፋትም ይህ ነው። "በመስከረም በዚህ ቀን ከተወለድክ እንዲህ አይነት ባህሪ ይኖርሃል፣ ማግባት ያለብህ በጥር በዚህ ቀን የተወለደ ሰውን ነው" የሚለው ተግባር ነው እግዚአብሔርም የማይወደው፣ ወደ ጥንቆላ ግብርም የሚገባው። በዘመናችንም "zodiac" የሚል የተሽሞነሞነ ስም ተሰጥቶት እንደ ህዳር ወረርስኝ የተስፋፋው። በርግጥ ዞዲያክ ሲባል 12 ከዋክብት አሉ ወይ? እውነት ነው። የየራሳቸው ወር አላቸው ወይ? ያም እውነት ነው። በመጽሐፈ ሄኖክም፣ በባሕረ ሀሳብም፣ እንደ ቻይና ባሉ የካላንደር ስረአቶችም አሉ። ነገር ግን ያንን ከጥንቆላ ጋር ማያያዙ፣ ኮከብህ ይህ ነው፣ ኮከብህ ከሱ ኮከብ ጋር ገጠመ ወዘተ የሚሉት ነገሮች ናቸው ችግር የሚፈጥሩት።

ይህንን በዚሁ ትተን ወደ ሌላው ስናልፍ ደግሞ ስር መቁረጥ የተባለ ግብር መላእክቱ ለሰዎች እንዳስተማሩ መጽሐፈ ሄኖክ ይነግረናል። ይህም እንደ ኮከብ ቆጠራው ሁሉ በሶስት ተከፍሎ ሊታይ ይችላል።

እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፦

- ለመድኃኒት የሚሆኑ ስሮች ወይም እፀዋት
- አደንዛዥ እፆች
- የጥንቆላ እፆች

የመጀመሪያውን ስንመለከት፣ ለተለያየ በሽታ መድኃኒት የሚሰራው ከእጽዋት ነው። ይህ ከጥንት ዘመን ጀምሮ በመላው ዓለም የነበረ እውነታ ነው። እንዲያውም በመጽሐፈ ኩፋሌ እንደሚነግረን፦ ከጎርፉ ዘመን በኋላ የኔፍሊም ቅሪቶች ወደ አጋንንት ተቀይረው የሰውን ልጆች በብሽታ ሲያሳምሙ፣ እግዚአብሔር ለኖህ የተለያዩ መድኃኒት የሚሆኑ እፆችን ነግሮታል። ኖህም በጽሑፍ አስቀምጦታል። በኛም ሀገር ከጥንት ጀምሮ አባቶች የተለያዩ ስራ ስሮችን ተጠቅመው በሽታን ያድናሉ። ይህም ማለት እውቀቱ ከጥንት ጀምሮ ለሰው ዘር በሙሉ ተሰጥቶ ነበር፣ ያም ለአባቶቻችን ደርሷል።

ታዲያ እዚህ ጋር የምናስተውለው ነገር፣ በሽታን የሚያመጡት አጋንንት በድሮ ዘመን ኔፍሊም የነበሩ፣ በኖህ ዘመንም ስጋ አካላቸው ተገፎ ወደ መናፍስት የተቀየሩ ናቸው ማለት ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ መድሃኒቱ ከእጽዋት የሚገኘው ኬሚካል መሆኑ፣ ያ ኬሚካል ወደ ሰውነታችን ሲገባም በነዚህ መናፍስት/ኔፍሊም ላይ ተጽዕኖ መፍጠር መቻሉ ነው። ይህም ወደ ቀጣዩ የእፆች ነገር ይወስደናል።

በዓለም በሙሉ የተለያዩ አደንዛዥ እና አነቃቂ እፆች አሉ። እንደ ሻይ፣ ቡና፣ ጫት፣ ትምባሆ፣ ሃሺሽ፣ ካናቢስ፣ የኦፒየም አበባ የመሳሰሉት ይገኛሉ። ጥንካሬያቸውም እጅግ ደካማ ከሆነው ሻይ ጀምሮ፣ መጠነኛ የሆነው ቡና፣ ከዚያም ከፍ ያሉት ጫት እና ትምባሆ፣ ከዚያም እጅግ አደገኛ የሆኑት ሃሺሽ፣ ካናቢስ እና ኦፒየም ይገኛሉ። እነዚህም ተጽዕኖአቸው በውስጣቸው ያለው ኬሚካል (ካፊን፣ ኒኮቲን፣ ኮኬን፣ ሄሮይን ወዘተ) የሚያመጣው መሆኑ፣ እነዚህ ኬሚካሎችም ወደ አእምሮአችን ገብተው የአእምሮአችን እጅግ ወሳኝ የሆነውን ዶፓሚን የሚቆጣጠሩ እና በዶፓሚን ላይ ባላቸው ተጽዕኖ ምክንያትም ሱስን እንደሚፈጥሩ በዘመናችን ሳይንስ ደርሶበታል። ነገር ግን ሳይንሱ ሳይታወቅ በፊትም በመላው ዓለም እነዚህን እጽዋት መጠቀም የተለመደ ነው። ለሺዎች ዘመናትም ሰዎች በተመሳሳይ መልኩ ተጠቅመዋቸዋል።

አንዱ የሚታወቅ የነዚህ እፆች በተለይ ጠንከር ያሉት ንቃተ ህሊናችንን የመለወጥ ባህሪ አላቸው። ይህም ክስተት "Altered State of Consciousness" ይባላል። ይህም ክስተት እፁን የወሰዱ ሰዎች የተለያዩ ነገሮች እንደሚታያቸው ይጠቅሳሉ። አንዳንድ ለረጅም ዘመናት የወሰዱ ሰዎችም መናፍስትን፣ ኔፍሊሞችን ጭምር ማየት እንደቻሉ በተደጋጋሚ ይናገራሉ። ከዚህ ውጪ ይህ altered state ሌሎች ተጽዕኖዎች አለው። ሰዎቾ አእምሮአቸው ድሮ ከነበረው ደረጃ በላይ እንዲጠቀሙ እና ከፍ ያለ አረዳድ እንዲኖራቸው እንዳደረገ የሚናገሩ ብዙ ናቸው። በሀገራችንም ለጥናት ይጠቅማል ብለው ጫት የጀመሩ ብዙ ሰዎች አሉ። በውጪውም ዓለም በሲልከን ቫሊ ያሉ ሰዎች እንደ LSD ያሉ እፆችን ከወሰዱ በኋላ የፈጠራ ችሎታቸው እንደ ጨመረ እና የቴክኖሎጂ መፍጠር ችሎታቸውን እንዳሳደገው በተደጋጋሚ ያነሳሉ።

ከዚህ ውጪ "altered state" የጥንት ህዝቦች፣ በተለይ ነጮች ወደ ጦርነት ከመሄዳቸው በፊት ይጠቀሙበት ነበር። እፅን ከወሰዱ በኋላ እጅግ ከፍተኛ የሞራል ደረጃ ላይ ይደርሳሉ፣ ከፍተኛ የጩኸት እና በሞራል የመነሳሳት ነገር ያሳያሉ፣ ፍርሃታቸውም ፈጽሞ ይጠፋል፣ በዚህም ምክንያት ወደ ጦርነት ሲገቡ እጅግ አስፈሪ ሆነው ነው። ይህም ሁኔታ "frenzy" ይባላል። በተለይ በዚህ frenzy ክስተት የሚታወቁት በአውሮፓ ታሪክ አጅግ አስፈሪ ተዋጊ የነበሩት የቫይኪንግ ህዝቦች ናቸው። እነሱም በዚህ "frenzy" ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ያለ ምንም ፍርሃት ወደ ውጊያ የሚሄዱትን ሰዎቻቸውን የሚጠሩበት "Berserker" የተባለ አጠራር ነበራቸው።

የቫይኪንግ "Berserk" ተዋጊዎች

ሌላኛው ደግሞ እነዚህን እፆች ለተለያዩ ለአምልኮ ስርአቶች የሚጠቀሙ ባህሎች አሉ። በኤሺያ እና በተለይም ላቲን አሜሪካ እነዚህ ባህሎች ይታወቃሉ። በነዚህ የአምልኮ ስርአቶች (rituals) ሰዎቹ ከበሮ እየተመታ እና ሙዚቃ እየተደረገ እጅግ አደገኛ የሆነውን እጽ ይወስዱ ነበር። በዚህም ጊዜ "altered state" ላይ ይደርሳሉ፣ እና ከአጋንንት ጋርም ይገናኛሉ። አጋንንቱም የተለያየ ደስ የሚል ነገር ይነግሯቸዋል። ከአማልክቶቻችሁ ጋር ተገናኛችሁ ይሏቸዋል። አንዳንዴ እንደውም "እናንተ ራሳችሁ አማልክት ናችሁ" ይሏቸውና እፁንም ከወሰዱ በኋላ "በውስጤ ያለውን አምላክ አገኘሁት" ብለው እንዲያስቡ ያደርጓቸዋል። የአምልኮው ስርአት መሪዎችም የዛ ሃይማኖት መሪዎች ሆነው አምልኮው ለዘመናት እንዲቆይ ያደርጉታል።

ከዚህ ጋር የሚመሳሉ ስርአቶ በመላው ዓለም ነበሩ (አሁንም አሉ)። ለምሳሌ በህንድ ሺቫ የሚባለው እና በግሪክ ዲዮኒሰስ/ባከስ የተባለው አምላክ የሚመለኩበት መንገድ ተመሳሳይ ነበር። ዘፈን እየዘፈኑ እና እየጨፈሩ እፅ/መጠጥ መውሰድ፣ ከዚያም የተለያዩ ልቅ ወሲብ ተግባርን የመፈጸም ባህል ነበር። በተለይ በግሪኮች ዘመን ይህ የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጭምር ጠቅሶታል። ይህም በገላትያ መልእክት 5፥21 ላይ ከጠቀሳቸው ተግባራት ውስጥ "ዘፋኝነት" ያለው ነው። ያ ቃል በአማርኛ አቻ ስሌለው "ዘፋኝነት" ተብሎ ተተረጎመ። ነገር ግን የኢንግሊዘኛ ቃሉ "revelry" ነው። ይህም የተጠቀሰው ተግባር ሰዎች ያንን የአምልኮ ስርአት ከተሳተፉ በኋላ በስካር ውስጥ ሆነው፣ በከፊል እርቃናቸው በከተማው እየዘፈኑ የሚሮጡበት ነው።

ታዲያ ይህ ተግባር በዘመናችንም ተለምዷል። ወጣቱ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ዘንድ ይሄዳል። ይጠጣል፣ ሰክሮም በልቅ ወሲብ ይሳተፋል። "party" በሚል ቃልም ይህን ልቅ ሰይጣናዊ ግብር ለማሳመር ይሞክራል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ደግሞ አንድ አደገኛ ነገር አለ።

EDM የተባለው የሚዚቃ አይነት፣ በተለየ ዜማው እና የከበሮ ድምጹ ይታወቃል። በሀገራችን እንደ ሮፍናን ያሉ ሰዎች የሚያቀርቡት ማለት ነው። በውጪው ዓለም የዚኛውን ሙዚቃ ኮንሰርት የሚሄዱት በተለየ ሁኔታ ነው። አደንዛዥ እፅን እጅግ ይወስዳሉ። እናም የሚወስዷቸው እፆች "psychedelic" በሚባለው ዘርፍ የሚመደቡ ናቸው። ይህም እፁን ወስደው ያንን ሙዚቃ ሲያዳምጡ የሚሆኑበት የንቃተ ህሊና ሁኔታ "trance" የሚባል ሲሆን አእምሮአችን በዚያ ሁኔታ ውስጥ ባለበት ጊዜ አድርግ የተባለውን ሁሉ እሺ ብሎ ይቀበላል። እናም subconscious በሆነ መልኩ መልእክቶች ከተላለፉለት ይቀበላል።

ይህ ሁሉ ታዲያ በጥንቶ በኔፍሊሞና በወደቁት መላእክት ዘመን የነበረ፣ ከጎርፉ ዘመን አልፎም ለዚህ ዘመን የደረሰ ነው። ታዲያ አብሮትም የጣዖት አምልኮ የመጣ መሆኑ ግልጽ ነው። እነዚህ ሁሉ አምልኮዎች ጣዖት አምልኮ መሆናቸውን የሚያሳየው ይህ ነው። እነዚያ የወደቁት መላእክት እና ኔፍሊም ከሰዎች የሚበልጥ ቁመት፣ አካል፣ የአእምሮ ብቃት፣ እውቀት ነበራቸው። ስለዚህም የሰው ልጆች ከኛ በታች ናቸው፣ ሊያመልኩን ይገባል ብለው ማሰብ ጀመሩ። ከዚያም መላው ዓለም እግዚአብሔርን ማምለክ ትቶ እነሱን ማምለክ ጀመረ። ይህም አምልኮ ከሙዚቃ እና እፆች የታጀበ ስርአት ሆነ። ከጎርፉ ዘመን በኋላም ያ አምልኮ በጣዖት መልኩ ተመለሰ። ጣዖታቱም በዚያ ዘመን የነበሩትን የኔፍሊም ታሪክ በአፈ-ታሪክ መልኩ የሚታወሱ ሆኑ።

ሌላው በመጽሐፈ ሄኖክ የተነገረው ደግሞ በእንስሳት ላይ የተሰራ ስራ ነው። ይህንንም በሁለት መልኩ ማየት እንችላለን።

- የዘር ማዳቀል ስራ
- ከእንስሳት ጋር ግንኙነት መፈጸም

መጽሐፈ ሄኖክ የሚነግረን በሁሉም እንስሳት፣ አሳ እና በሆዱ የሚሳበውን ጨምሮ፣ በነሱ ላይ ኃጢአት እንደተሰራ ይነግረናል። ይህ የሚያመላክተን እነዚህ ኔፍሊሞች የእንስሳትን ዘር እንዳቀላቀሉ ነው። ማዳቀል ስንልም የማይገኙ እንስሳትን፣ ለምሳሌ ፈረስ እና አሞራ፣ ድመት እና ውሻ፣ እንደዛ አይነት ነገሮችን ነው። ስለዚህ ዘር የማዳቀል ሳይንስ የተጀመረው በኛ ዘመን ሳይሆን፣ በዚያ በጥንት እና ሩቅ ዘመን ነው። በዚህም ምክንያት በመላው ዓለም የተለያሉ አፈታሪኮች እንደ "Griffin" (የአሞራ ራስ እና ክንፍ፣ የፈረስ አካል) "Sphynx" (አንበሳ ራስ፣ የአሞራ ክንፍ) ወዘተ በዚህ ምክንያት ሊኖሩ ቻሉ።

ሌላኛው ደግሞ፣ እነዚህ ኔፍሊሞች በኃጢአት እጅግ የዘቀጡ እና እግዚአብሔርንም ፍጹም የሚጻረሩ ከመሆናቸው የተነሳ ከእንስሳት ጋር ግንኙነት መፈጸማቸው ነው።

ከእንስሳት ጋር ግኝኙነት መፈጸማቸው ደግሞ ሌላም ብዙ ያልተረዳነው ምክንያት ሊኖረው ይችላል። ይኸውም፣ ምናልባት፣ የወደቁት መላእክት ራሳቸው ስጋቸው በከፊል የእንስሳ ቢኖረውስ?

ከዚያም በላይ ግን፣ መላእክት ራሳቸው የእንስሳ መሰል አካል ቢኖራቸውስ። ያም ብቻ ሳይሆን፣ እንስሳት ራሳቸው የተፈጠሩት በመላእክት ገጽ እና መልክ ቢሆንስ? እኛ የተፈጠርነው በእግዚአብሔር መልክ እንደሆነ ሁሉ እንስሳት የተፈጠሩት ደግሞ በመላእክት መልክ ቢሆንስ? ይህንን ለመረዳት የኪሩብ መልአክን እንመልከት። መላእክቱ 4 ገጽ አላቸው። ከአራቱ አንዱ የሰው፣ ሶስቱ የእንስሳ ነው። እነዚህ የኪሩብ መላእክትም የራሳቸው ነገድ አላቸው። ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ከነዚህ መላእክት አራቱ ተመርጠው ነው የስላሴን መንበር እንዲሸከሙ የተደረጉት። እንጂ ሌሎች እጅግ ብዙ ኪሩብ መላእከት አሉ። ስለዚህ ከነሱ ውስጥ ከፊሉ ከእነ አዛዝኤል ጋር ወደ ምድር ወድቀው ቢሆን፣ እንደ እኛ ስጋ ሲሰጣቸው፣ ስጋቸውም በከፊል የእንስሳት አካልም ሊኖራቸው ይችላል። ያም ማለት ልጆቻቸው ኔፍሊሞች ሲወለዱ፣ ያንን የእንስሳነት አካል በከፊል ይዘው ይወለዳሉ። እናም የሰው ልጅ ሌላ ሰውን ሲያይ ለግንኙነት እንደሚመኘው ሁሉ፣ እነሱም ከፊል እንስሳ በመሆናቸው እንስሳትን ለግንኙነት ፈልገው ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት ከፊል ሰው፣ ከፊል እንስሳ የሆኑ ፍጥረቶች እጅግ በዝተው ይሆናል።

ይህንንም የሚያሳየን ከጎርፉ ዘመን በኋላም እንዲህ አይነት ፍጥረቶች ብዙ አፈታሪኮች ላይ መገኘታቸው ነው። በጥንት ግብጽ ሃይማኖት ሰው+አሞራ፣ ሰው+በሬ፣ ሰው+ውሻ የሆኑ አማልክት ነበራቸው። በግሪክ አፈ-ታሪክ ሰው+ፈረስ የሆኑ ነበሩ።
Horus (ሰው እና ወፍ) እና Anubis (ሰው እና ውሻ የሆነው)


Centaur (ሰው እና ፈረስ)


ከአፈ ታሪክ ስንወጣ እንኳን፣ በቤተክርስቲያን ታሪክ ከፊል ሰው ከፊል ውሻ የሆኑ ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ በሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ታሪክ እናገኛቸዋለን። በውጪው ዓለምሞ "Saint Christopher the dog head" የተባለ ከአንገት በታች ሰው፣ ከአንገት በላይ ውሻ የሆነ ቅዱስ አለ።

የውሻ አካል ያለው ክሪስቶፈር የተባለው ቅዱስ

እነዚህ ነገሮች ተራ አፈ ታሪክ ወይም ፈጠራ ሳይሆኑ፣ በአንድ ዘመን የነበረን እና ወደ ዘመናችን የመጣን እውነታ የሚያመላክቱ ናቸው።

ይህንን ካልን በኋላ፣ ከነዚህ እውቀቶች ጠቃሚ ነበሩ የምንላቸውን እንጥቀስ። የመአድን ማውጣት እውቀት፣ የከዋክብት ቆጠራ ለካላንደር እና ባሕርተኞችን አቅጣጫ የሚያሳየው፣ ዕንቁዎችን ለመልካም መጠቀም፣ እፆችን ለመድኃኒት መጠቀም መልካም ነገሮች ነበሩ። የሰው ልጅም ይህንን የተፈጠረበትን ዓለም ተጠቅሞ ህይወቱን ማሻሻል፣ የተሻለ ኑሮ መኖርን እንዲችል ማድረጉ መልካም ነገሮች ነበሩ። የተቀሩት ግን የሰው ልጅን ወደ ዓመጻ፣ ዝሙት፣ ባእድ አምልኮ፣ ጥንቆላ ያስገቡ ክፉ ምግባሮች እና እውቀቶች ነበሩ።

Post a Comment

0 Comments